ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከስዊድን የሰላም፣ ደህንነትና ልማት ተቋም ጋር በትብብር ለመስራት ተስማማ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ከስዊድን የሰላም፣ ደህንነትና ልማት ተቋም ከሆነው ኤፍ ቢ ኤ ጋር የቀድሞ ታጣቂዎች መልሶ ማቋቋም ፕሮግራም አተገባበር ዙሪያ አብሮ መስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተመስገን ጥላሁን በዚህ ወቅት÷ የስዊድን መንግስት ለፕሮግራሙ ትግበራ እያደረገ ያለውን የገንዘብ ድጋፍ አድንቀዋል።
ስምምነቱ ለተቋማዊ አቅም ግንባታ፣ ለምርምር እንዲሁም ዓለም አቀፍ ልምድ ለመቅሰም ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ገልጸዋል፡፡
ፕሮግራሙን በዘላቂነትና መንግስት በያዘው ጊዜ ለማጠናቀቅ የስዊድን መንግስት የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥልም መጠየቃቸውን የኮሚሽኑ መረጃ አመላክቷል፡፡
የተቋሙ ጀነራል ዳይሬክተር ፐር ኦልሰን በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ ውጤታማ የዲሞቢላይዜሽን እና መልሶ ማቋቋም ሥራ በጋራ ለማከናወን ስምምነቱ መሠረት እንደሚጥልና ትብብሩንም ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር ገልጸዋል፡፡