የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የማህበራዊ ጥበቃ ስራ ስኬታማ መሆኑን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 18፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳዮች ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከዓለም ባንክ የአፍሪካ ቀንድ ዳይሬክተር ማርያም ሳሊም ጋር በማህበራዊ ጥበቃና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
በወይይታቸውም÷ በማህበራዊ ጥበቃ ዘርፍ እየተከናወኑ ባሉ ተግባራትና በአዳዲስ የትብብር መስኮች ዙሪያ የሁለቱን ወገኖች አጋርነት የበለጠ ስለማጠናከር መክረዋል፡፡
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ መንግስት ለችግር ተጋላጭ ዜጎችን ህይወት በዘላቂነት ለመለወጥ እንዲያስችል የከተማና የገጠር ልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራሞችን ከባንኩ ጋር በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሯ በበኩላቸው፥ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የማህበራዊ ጥበቃ ስራ ስኬታማና ለሌሎች ሀገራት ጭምር ተሞክሮ ሊሆን እንደሚችል ባደረጉት ጉብኝት መመልከታቸውን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ የሚያካሂደውን የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት የበለጠ ለማጠናከርና ቀጣይ ፕሮግራም ቀረጻዎች ላይ የዓለም ባንክ በጋራ እንደሚሰራም ተናግረዋል።