የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምባላላ በዓል እየተከበረ ነው
አቶ ደስታ ሌዳሞ በበዓሉ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ በዓለማችን የራሳቸዉ አቆጣጠር ያላቸዉ ህዝቦች ጥቂት ሲሆኑ፤ ከጥቂቶቹም አንዱ የሲዳማ ህዝብ ነው ብለዋል፡፡
የሲዳማ አያንቱዎች ተፈጥሮ የሰጠቻቸዉን ዕዉቀት በመረዳት የፊቼ ጫምባላላን ቀን የሲዳማ ብሔር የዘመን መለወጫ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡
የፊቼ ጫምባላላ በዓል የመደመር፣ የመከባበር፣ የአንድነት መሰረት ያላቸዉ ዕሴቶችን የያዘ በመሆኑ በዓሉን ለማህበረሰቦች ትስስር መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው÷ ስለጊዜ የሚረዳ ህዝብ በጥልቅ ፍልስፍና የሚኖርና በእዉቀት የሚመራ ህዝብ ነዉ ብለዋል፡፡
የፊቼ ጫምባላላ በዓል የሲዳማ ህዝብ በዚህ ዕዉቀት በመመራት ለኢትዮጵያ ብልፅግና ያበረከተዉ ውድ ሀገር በቀል በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ÷ ከሲዳማ ህዝብ ጋር የፊቼ ጫምባላላን በዓል ለማክበር በሶሬሳ ጉዱማሌ በመገኘታችን ደስታችን ትልቅ ነው ብለዋል፡፡
በምንተስኖት ሙሉጌታ