Fana: At a Speed of Life!

በሽግግር ፍትህ ፖሊሲው መሰረት ነፃ እና ገለልተኛ ልዩ ችሎት ለማቋቋም ህግ እየተረቀቀ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ላይ በተመለከተው አግባብ ነፃ እና ገለልተኛ ልዩ ችሎት ለማቋቋም የህግ ማርቀቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ገለጸ።

በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉብኝት ላደረጉት በኢትዮጵያ የፈረንሳይ አምባሳደር አሌክስ ላሜክ፤ በኢትዮጵያ የሽግግር ፍትህ ፖሊሲን መሰረት አድርጎ ልዩ ችሎት የማቋቋም ሂደትን በተመለከተ እንዲሁም በሌሎች የሪፎርም ሥራዎች ዙሪያ ገለፃ ተደርጓል።

የሽግግር ፍትህ ፖሊሲ ትግበራ ላይ ፍርድ ቤቶች የተሰጣቸውን ሚና ለመተግበር በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ትብብር ማድረግ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይም ውይይቶች ተካሂደዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት ቴዎድሮስ ምህረት የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት በሽግግር ፍትህ ፖሊሲው ላይ በተመለከተው አግባብ ነፃ እና ገለልተኛ ልዩ ችሎት ለማቋቋም የህግ ማርቀቅ ሥራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ችሎቱን የማደራጀት ተግባር የፍርድ ቤቱ ኃላፊነት መሆኑን በማንሳት፤ ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከመላኩ በፊት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር የህዝብ ውይይት ለማድረግ በዝግጅት እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

አምባሳደር አሌክስ ላሜክ በበኩላቸው፤ ከእውነት ማፈላለግ ጋር በተገናኘ ከተጎጂዎች ጋር ውይይት ስለሚደረግበትና ተጠያቂነትም ስለሚታይበት መንገድ ሀገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ መግለጻቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍ/ቤት መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.