ሚኒስቴሩ ከብርቱካን ተመስገን ከበደ ጋር በተያያዘ ማብራሪያ ሰጥቷል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሰሞኑን በማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ በሆነችው ብርቱካን ተመስገን ከበደ የትምህርት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ትምህርት ሚኒስቴር ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡
የማብራሪያው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ስለሆነችው ብርቱካን ተመስገን ከበደ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት ስላለው ማብራሪያ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በስም ተጠቃሽ በ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ተማሪ የነበረች ቢሆንም የብሄራዊ ፈተናው በወቅቱ በተፈጠረው ዓለም ዓቀፍ የኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 02/2013 ዓ.ም እንዲሰጥ መደረጉ ይታወሳል።
ተማሪዋም በዚሁ ጊዜ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን በሞጣ መሰናዶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፈተና ወስዳ 392 ውጤት በማምጣት በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመን ሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ምደባ ተደርጎላታል፡፡
ሆኖም ግን ወደተመደበችበት ዩኒቨርሲቲ ያልሄደችና ያልተመዘገበች ሲሆን ወደ ሀዋሳ ከተማ በማቅናት በተከታታይ የትምህርት ኘሮግራም (ኤክስቴንሽን) ተመዝግባ “በአካውንቲንግና ፋይናንስ” የትምህርት ክፍል በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ ኘሮግራም ከግቢ ውጭ ሆና ትምህርቷን ስትከታተል የነበረችና ትምህርቷንም ሳትጨርስ ያቋረጠች መሆኑን ከሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የተገኘ መረጃ ያረጋግጣል፡፡
በተቃራኒው በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ስርጭት በተላለፈው ፕሮግራም ግለሰቧ በሀሮማያ ዩኒቨርስቲ ተመድባ ወደ ሀሮማያ በመጓዝ ላይ ሳለች አውቶቡስ ውስጥ ባገኘቻት ደምቢደሎ ዩኒቨርስቲ ተመድባ በመጓዝ ላይ ካለች ሌላ ተማሪ ጋር በመነጋገር ሀሮማያ ዩኒቨርስቲ የነበራትን ጉዞ በመሰረዝ ወደ ደምቢደሎ ዩኒቨርስቲ ሄዳ ለመማር ተመዝግቢያለሁ ማለቷ ከእውነታውና ከአሰራር ውጭ የሆነና በፍጹም ወደ ደምቢደሎ ዩኒቨርስቲ ያልሄደችና ምዝገባም ያላደረገች መሆኑ የዩኒቨርስቲው መረጃ ያስረዳል።
በዚህ አጋጣሚ ማንኛውም አይነት የአዲስ ተማሪዎች ምደባ የሚከናወነው በትምህርት ሚኒስቴር ብቻ እንጂ በዩኒቨርስቲዎች ደረጃ የማይፈቀድ መሆኑም ለማሳዎቅ እንወዳለን።
በመሆኑም፤
1. በማህበራዊ ሚዲያው እየተሰራጩ ያሉ መረጃዎች በከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ጋር ካለው እውነታ ውጪ የሆነ መሆኑን እንገልጻለን፤ ይህንኑ የሚያረጋግጡ መረጃዎችም ከዚህ ማብራሪያ ጋር ተያይዘዋል፤
2. ይህንን የተሳሳተ መረጃ መሰረት በማድረግ በውስን ዩኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ስራውን ለማስተጓጎል የተለያዩ ሙከራዎች ተደርገዋል፡፡ እንደሚታወቀው የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች የሚከናወኑባቸው፣ እውቀትና እውነት የሚሰርጽባቸው በእውነትና በእውቀት የሚመሩ አለም ዓቀፍ ተቋማት መሆናቸው ሊታዎቅ ይገባል።
3. የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (EBS) ከዚህ ቀደም እንደሚያደርገው እንደማንኛውም ሚዲያ ጉዳዩን ከማሰራጨቱ በፊት ከዩኒቨሲቲዎቹ ወይንም ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘውን መረጃ ማጣራት ሲገባው ይህንን ጉዳይ ሳያጣራ በቀጥታ አየር ላይ ማዋሉ ህዝቡን ከማሳሳት ባሻገር የዩኒቨርስቲዎቹን ገጽታ በማበላሸትና በማጠልሽት ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ በመሆኑ ሃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል።
ስለሆነም እንደዚህ አይነት የፈጠራና የሀሰት ቅንብሮችን መሰረት አድርጎ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ የሚደረግ የመማር ማስተማር እንዲሁም የምርምር ስራዎቻቸውን ሊያውኩ የሚችሉ ማንኛውም አይነት እንቅስቃሴና ተግባር ፍፁም ተቀባይነት የሌላቸውና ይህንንም ሆን ብለው በሚፈጽሙና በሚገፉ አካላት ላይ ከፍተኛ አሰተዳደራዊ እርምጃ አለፍ ሲልም በተቋማቱ ንብረትም ሆነ በሰው ላይ ለሚደርስ አደጋና ጉዳት ህጋዊ እርምጃ የሚወሰድ መሆኑን ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ማሳሰብ ይወዳል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ የዩኒቨርሲቲዎች እና የአካባቢው ማህበረሰብ እንዲሁም ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲዎች የተቋቋሙበት መሰረታዊ ተልዕኮዎች በመረዳት የተቋማቱን ደህንነትና ቀጣይነት ለማረጋገጥ ተገቢውን ጥበቃ እንድታደርጉ ከአደራ ጭምር እናሳስባለን፡፡