አምባሳደር ደሊል ከድር የሹመት ደብዳቤያቸውን ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ አቀረቡ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በደቡብ አፍሪካ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ልዩ መልዕክተኛ እና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ደሊል ከድር ለደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ የሹመት ደብዳቤያቸውን አቅርበዋል።
አምባሳደሩ በወቅቱ፤ በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት እና በፓን-አፍሪካኒዝም መርህ ላይ የተመሰረተውን የረጅም ጊዜ ታሪካዊ የወዳጅነትና ወንድማማችነት ግንኙነትን አንስተዋል።
እንዲሁም ሁለቱ ሀገራት ያላቸውን የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በተመለከተም ተናግረዋል።
ደቡብ አፍሪካ ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ የምታደርጋቸውን እንቅስቃሴዎች አድንቀዋል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረው ግጭት መቋጫ እንዲያገኝ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ሂደትን በማስተናገድ እና በማሰናዳት ላደረጉት ጉልህ አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
ለፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈጻሚነት የኢትዮጵያ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ እንደሚገኝ እና በዚሁ ዙሪያ በደቡብ አፍሪካ በኩል የተለመደው ድጋፍ እንደሚቀጥል ተስፋ እንዳላቸው መግለጻቸውን በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል።
በሚኖራቸው ቆይታም የኢትዮጵያን እና የደቡብ አፍሪካን ታሪካዊ ግንኙነት በንግድ፣ በኢንቨስትመንት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በባህል እንዲሁም በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የትብብር ዘርፎች አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ ለማድረግ እንደሚሰሩ ቁርጠኝነታቸውን ገልጸዋል።