የሎጂስቲክስ አገልግሎት ቀልጣፋና ዘመኑን የዋጀ እንዲሆን እየተሰራ ነው – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተወጣጡ 100 ወጣት ሴቶችን በሎጂስቲክስ ዘርፍ ማሰማራት የሚያስችል ሥልጠና ተጀምሯል፡፡
የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ ሎጂስቲክስ የሀገር ኢኮኖሚ የደም ስር በመሆኑ አገልግሎቱ ዘመኑን የዋጀና ቀልጣፋ ሊሆን ይገባል፡፡
ለዚህም የሰልጠነ የሰው ሃይል ማፍራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመው÷ወጣት ሴቶችን በሎጂስቲክስ ዘርፍ ለማሰማራት የተጀመረው ሥልጠና በዘርፉ ያለውን ክፍተት መሙላት ያስችላል ብለዋል፡፡
ስልጠናው ከሁሉም የኢትዮጵያ ማህበረሰብ የተወጣጡ ሴት ወጣቶችን ማካተቱን የገለጹት ሚኒስትሩ÷ሰልጣኞች ዘርፋን እንዲያውቁ እና የበለጠ እንዲመራመሩ አሳስበዋል።
ሰልጣኞች ከዚህ ቀደም በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተመረቁና ሥራ እያፈላለጉ የነበሩ መሆናቸው ተጠቁሟል።
ስልጠናው በሎጂስቲክስ ዘርፍ ያለውን የሰለጠነ የሰው ሃይል እጥረት ለመቅረፍ፣ የአገልግሎትና ተወዳዳሪነት ደረጃ ለማሳደግ፣ የስራ ዕድል ለመፍጠርና በዘርፉ የሴቶችን ተሳትፎ ለመጨመር ያለመ ነው ተብሏል፡፡
ወጣት ሴቶች ለስምንት ወራት ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ ወደ ሥራ እንዲሰማሩ ድጋፍ እንደሚደረግ መገለጹንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡