ጽንፈኞች ያስተላለፉት ሀሰተኛ መረጃ ዓላማ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መፍጠር ነው – አቶ መላኩ አለበል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ጽንፈኛ ሃይሎች ብርቱካን ተመስገንን በሚመለከት ያስተላለፉት የሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልም ዋነኛ ዓላማ ትርምስና ፖለቲካዊ አለመረጋጋት መፍጠር መሆኑን የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል ተናገሩ።
ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ሰሞነኛ የሀሰተኛ ፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎች አንድምታ በቀላሉ የሚታዩ ሳይሆን የፖለቲካ አለመረጋጋት መፍጠር፣ ህዝብን በህዝብ ላይ ማነሳሳትና ግጭት የመፍጠር እኩይ ዓላማ ያነገቡ ናቸው።
በኢቢኤስ ሚዲያ በኩል የተላለፈው የሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልም አንድምታም ሀሳብ ያለቀባቸው ኃይሎች የህዝብ ለህዝብ ግጭት፣ ጥርጣሬና ባላንጣነት የመፍጠር እኩይ ዓላማ ያለው መሆኑን ገልፀዋል።
በአማራ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ግጭት የገቡ አካላት መምህራንን ጨምሮ ንፁሃንን በጅምላ በመግደል ትውልድ አምካኝ፣ ሰላምና ልማትን የሚፃረር ተግባር ላይ መሰማራታቸውን መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
አሁን ደግሞ የክልሉ ህዝብ የጥፋት ኃይሎችን እኩይ ድርጊት እየተረዳ ሲመጣ ዘመቻ አንድነት በሚል ፕሮፓጋንዳ መክፈታቸውን ጠቅሰው፤ ለዚህም ህዝብን የሚያደናግር አጀንዳ እንደከፈቱ ነው ያነሱት።
ይህም ሚዲያን በመጠቀም ሀገራዊ ቀውስና ትርምስ የመፍጠር ግብ ያነገበ እንደሆነም ተናግረዋል።
በሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልሙ የተሰራጨው መረጃ ህዝብ በመንግሥት ላይ እንዲነሳ ለማድረግ ያለመ ቢሆንም በህዝቡ አስተዋይነት የከሸፈ መሆኑን ገልጸዋል።
ፅንፈኛ ኃይሎች ከማህበረሰቡ እሴት ውጭ የሆኑ በደሎች በህዝብ ላይ መፈፀማቸውን ገልፀው፤ የአንዲት ሴት ሀሰተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ዘጋቢ ፊልም ሰርቶ በማራገብ የፖለቲካ አለመረጋጋት የመፍጠር ስራ ላይ መሰማራታቸውን ጠቅሰዋል።
ሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልሙ ስለዜጎች ክብርና ነፃነት በመቆርቆር ሳይሆን ግጭት ለመቀስቀስና የህዝብ አንድነት ለመሸርሸር ያለመ ስለመሆኑም ገልፀዋል።
የአማራና ኦሮሞ ህዝብ ከማንም በላይ የተጋመደና የማይነጣጠል መሆኑን በመጥቀስ፤ የህዝብ አንድነት በየትኛውም ፅንፈኛ ቡድን እኩይ ሴራ የሚበጠስ እንዳልሆነ አንስተዋል።
በኢቢኤስ የተላለፈው ሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልም የጥፋት ሀይሎች በተቀናጀ መልኩ እንደሚሰሩና ለኢትዮጵያ ህዝብ እሴትና ክብር ያላቸውን ንቀት ያሳየ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች ሁሌም የህዝብ አንድነትን ለመሸርሸር እንደሚሰሩ ገልፀው፤ ህዝቡ እኩይ አጀንዳዎችን ወደ ጎን በመተው ከመንግሥት ጋር በመሆን ለሀገር ሰላምና ልማት እያደረገ ያለውን ተሳትፎ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።