Fana: At a Speed of Life!

ንጎሎ ካንቴ …

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በዓለም ከናኘበት ስኬት ላይ የመድረሱ ጉዞ የተጀመረው በፈረንጆቹ 1998 ፈረንሳይ ባሰናዳችው የዓለም ዋንጫ ነበር፡፡

ይህ ኮከብ በዓለም በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱ የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ስለመሆኑ መስካሪ አያሻውም፡፡

የታሪኩ ባለቤት ንጎሎ ኮንቴ በዛሬዋ ዕለት በፈረንጆቹ 1991 የተወለደ ሲሆን፥ በስደት ፈረንሳይ የገቡት ወላጆቹ የዘር ሐረጋቸው ከማሊ ይመዘዛል።

በእግር ኳስ ስኬታማ ስለመሆን የተለመበት የ1998ቱ የዓለም ዋንጫ ሀገሩ ፈረንሳይ ዚነዲን ዚዳንና ቲየሪ ሄንሪን በመሳሰሉ ከዋክብቷ ታግዛ ራሷ ያሰናዳችውን የዓለም ዋንጫ ከፍ አድርጋ ያነሳችበት ነበር፡፡

በወቅቱ ልቡ በኳስ ፍቅር የተነደፈችው ኮንቴ ከፓሪስ ወጣ ብላ በምትገኝ መንደር ጄኤስ ሱርስነር በሚባል አካዳሚ እግሮቹን ከኳስ ጋር አስተዋወቃቸው፡፡

በአካዳሚው ቆይታው ተስፈኛ ታዳጊ መሆኑን ቢያስመሰክርም በርካታ ክለቦች ተክለ ሰውነቱ ለኳስ ብቁ አይደለም በማለት እድል ሳይሰጡት ቀሩ፡፡

ሆኖም በፈረንጆቹ 2010 የቡሎኝን 2ኛ ቡድን በመቀላቀል፥ በኋላም በ2012 ለዋናው ቡድን ተሰልፎ በመጫወት የፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋችነት ጉዞውን ሀ ብሎ ጀመረ፡፡

ከዚያም በሌላኛው የፈረንሳይ ክለብ ኮን በሊግ-2 እና በሊግ ኧ ብቃቱን በማሳየት ይበልጥ ወደታወቀበት ሌስተር ሲቲ አቅንቷል፡፡

አንዳች የድካም ስሜት የማይታይበት ንጎሎ ኮንቴ ሳይጠበቅ የፕሪሚየር ሊጉ ባለክብር መሆን በቻለው የ2015/16ቱ የክላውዲዮ ራኔሪው ሌስተር ሲቲ ስኬታማ ዓመት አበርክቶው የጎላ ነበር፡፡

ራኔሪ በአንድ ወቅት ስለ ኮንቴ ሲናገሩ፡ ‹‹በቁምጣው ውስጥ ባትሪ አድርጎ የሚጫወት ነው የሚመስለኝ … መሮጥ አይታክተውም… እንዲያውም ብዙ ግዜ መሮጥ እንዲቀንስ እነግረዋለሁ›› ብለው ነበር፡፡

ከዚያ በኋላ በተክለሰውነቱ ምክንያት እምነት ታጥቶበት የነበረው ኮከብ በርካታ ክለቦች ዐይናቸውን ቢጥሉበትም ቀጣይ ማረፊያው ስታምፎርድ ብሪጅ ሆነ፡፡

ቼልሲን በተቀላቀለበት የመጀመሪያ ዓመት ዳግም የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማሳካት ሌላ ታሪክ መጻፍ ቻለ፡፡

በዚያው ዓመት የፕሪሚየር ሊጉ፣ የፕሮፌሽናል ተጫዋቾች ማህበር እንዲሁም የእግር ኳስ ጸሃፊያን ማህበር የዓመቱ ምርጥ ተጫዋች በመሆን ሶስት ሽልማቶችን አሸንፏል፡፡

ከፕሪሚየር ሊጉ በተጨማሪ በ2020/21 የቻምፒየንስ ሊግ፣ በ2021 የሱፐር ካፕ እና የዓለም ክለቦች ዋንጫ፣ በ2017/18 የኤፍ ኤ እና በ2018/19 የዩሮፓ ሊግ ዋንጫዎችን ከሰማያዊዎቹ ጋር አሳክቷል፡፡

ከክለብ ስኬቱ ባሻገር ያኔ ገና በልጅነቱ የተመኘውን የዓለም ዋንጫ በ2018 ከፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ጋር ለመሳም ችሏል፡፡

ኮንቴ አሁን ላይ ክሪስትያኖ ሮናልዶን ጨምሮ በርካታ ከዋክብትን ባሰባሰበው የሳዑዲ ፕሮ ሊግ ለአል ኢትሃድ እየተጫወተም ይገኛል፡፡

ለኳስ ብቻ ሳይሆን ለነፍስም የተሰጠው ንጎሎ ኮንቴ ከእግር ኳስ ስኬቱ ባሻገር በበጎ አድራጎት ተግባራት ለብዙዎች ተስፋን እየፈነጠቀ ይገኛል፡፡

ወደ ወላጆቹ የትውልድ ሀገር ማሊ በማቅናት በድህነት ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች ድጋፍ በማድረግ ላይ ሲሆን፤ በዚሁ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ በተለይ ለጤና እና ለትምህርት ተቋማት ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑ ይነገራል፡፡

በኃይለማርያም ተገኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.