በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሰለጠኑ የሁለተኛ ዙር ሰልጣኞች ተመረቁ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክኅሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በ17 የሙያ ዘርፎች ያሰለጠናቸውን የሁለተኛ ዙር ሰልጣኞች አስመረቀ፡፡
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ሌሎች የአሥተዳደሩ ከፍተኛ መአራሮች ተገኝተዋል፡፡
ከንቲባዋ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ ለተለያዩ ማኅበራዊ ችግሮች ተጋላጭ የሆኑ ዕድሉን ካገኙ ለውጥ ማምጣት እንደሚችሉ የዛሬ ተመራቂዎች ማሳያ ናቸው።
ተመራቂ ሰልጣኞች ወደ ሥራ በሚሰማሩበት ወቅት የሚገጥማቸውን ፈተና በመሻገር ለሎችም ምሳሌ ለመሆን በትጋት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
ሰልጣኞቹ ለወራት በመረጡት ሙያ ስልጠናቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸው የተገለጸ ሲሆን፤ ስልጠናውን ከወሰዱት 380 ሰልጣኞች መካከል 93 በመቶ ያህሉ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ምዘና (ሲኦሲ) ማለፋቸው ተጠቅሷል፡፡
ስልጠናቸውን ያጠናቀቁ ሰልጣኞች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ማዕከሉ ከተለያዩ ተቋማት ጋር እየሠራ መሆኑን አስታውቋል፡፡
በተጨማሪም ለሦስተኛ ዙር ስልጠና 1 ሺህ ሰልጣኞችን ለመቀበል ዝግጁ መሆናቸውን ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶ እና ክኅሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ዳይሬክተር ሂርጳ ጫላ (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡
በቅድስት ብርሃኑ