Fana: At a Speed of Life!

የፖለቲካ ሐሳብ ያለው ቡድን በሰላማዊ መንገድ በፖለቲካው መድረክ እንዲወዳደር በሩ ክፍት ነው – ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መንግሥት የትኛውም የፖለቲካ ሐሳብ ያለውን ቡድን በሐሳብ ሙግት እና ሰላማዊ መንገድ በፖለቲካው መድረክ እንዲወዳደር በሩን ክፍት አድርጓል ሲሉ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከሰሞኑ ብርቱካን ተመስገን የተባለችን ግለሰብን በመጠቀም የተሰራጨው የሐሰት ድራማ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ ግለሰቧን መጠቀሚያ በማድረግ የተላለፈው የሴራ ታሪክ መጠፋፋትን አልመው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች የግጭት ዕቅድ ነበር ብለዋል።

እነዚህ ኃይሎች ሐሰተኛውን ድራማ የብሔር ሽፋን በማልበስ እልቂት እንዲከሰት አልመው እንደነበርም ጠቁመዋል።

መንግሥት በአማራ ክልል ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ባካሄዳቸው ውይይቶች ማሕበረሰቡ ቅድሚያ ለሰላም እንደሚሰጥና የመጠፋፋት አካሄድን እንደማይደግፍ ማረጋገጡን አስታውሰዋል።

ይህንን የሕዝብ ፍላጎት መተግበር የማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎች የተጠቀሙት የሰሞኑ ድራማም የሕዝብ ድጋፍ ለማግኘት የስሜት መቆስቆሻ ለማድረግ አስበው እንዳቀናበሩት ገልፀዋል።

ነገር ግን ጊዜያዊ ችግሮችን በብልሀት የመሻገር ጥበብ ባዳበረው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት ሴራው ሊከሽፍ ችልሏ ነው ያሉት፡፡

በሁሉም ክልሎች ዘርፈብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩም፤ በሰላማዊና በማያጠፋፋ መንገድ ችግሮች እንዲፈቱ የሕዝቡ ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡

ሀገሪቱን ብዙ ዋጋ ካስከፈላት የመጠፋፋት ፖለቲካ ለመውጣት ሚዲያዎች ሁሌም ሀገርና ትውልድን ማስቀደም እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።

ፖለቲካችን ኢትዮጵያዊ አንድነትና ኅብረታችንን የሚንድ እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

መንግሥት የትኛውም የፖለቲካ ሐሳብ ያለውን ቡድን በሐሳብ ሙግት እና ሰላማዊ መንገድ በፖለቲካው መድረክ እንዲወዳደር በሩን ክፍት ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.