Fana: At a Speed of Life!

በረመዳን ወር የተገኘውን መንፈሳዊ በረከት ማስቀጠል ከሁሉም ሙስሊም ይጠበቃል- ጉባዔው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በረመዳን ወር የተገኘውን መንፈሳዊ በረከት፣ ትህትና፣ ፍቅር እና አንድነት ጠብቆ ማስቀጠል ፈጣሪ ከሁሉም ሙስሊም የሚጠብቀው ተግባር ነው ሲል የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ገለጸ፡፡

ጉባው 1 ሺህ 446ኛው የኢድ አል-ፊጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመላው ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

በመልዕክቱም፤ በመላው ሙስሊም ዘንድ በናፍቆት የሚጠበቀው የረመዳን ወር የጀሃነም በሮች የሚዘጉበት እና የጀነት በሮች የሚከፈቱበት የእዝነት፤ የጸጋ እና የመንፈሳዊ በረከት ወር መሆኑን ገልጿል።

ወሩ ሙስሊም ወገኖች በጾም እና በዱዓ ወደ ፈጣሪያቸው አብዝተው የሚቀርቡበት፤ ፍቅር እና መተሳሰብ የሚሰፍንበት፣ ርህራሄ እና በጎነት የሚልቅበት፤ ወንድማማችነት፣ መረዳዳት እና ሰላም የሚስፋፋበት ታላቅ የጸጋ ወቅት ነው ብሏል።

በረመዳን ወር የተገኘውን መንፈሳዊ በረከት፣ ትህትና፣ ፍቅር እና አንድነት ጠብቆ ማስቀጠል ፈጣሪ ከሁሉም ሙስሊም የሚጠብቀው ተግባር ነው ያለው ጉባኤው፤ ከመንፈሳዊ ከፍታ ሳይወርዱ ሁልጊዜ ሕይወትን በመርህ መምራት አስፈላጊ መሆኑን አመላክቷል።

ማህበረሰቡ የኢድ አል-ፊጥር በዓልን ሲያከብር እንደተለመደው ለሀገር ሰላም እና ዕድገት እንዲሁም ለሕዝቦች አንድነት ዱዓ በማድረግ፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ፣ የታመሙትን እና በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙትን ደግሞ በመጠየቅ ሊሆን እንደሚገባም አሳስቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.