Fana: At a Speed of Life!

የዒድ አል ፈጥር ዕሴቶች ለሀገር ግንባታ አስፈላጊ ናቸው- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዒድ አል ፈጥር ዕሴቶች ለሀገር ግንባታ አስፈላጊ ናቸው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም፤ እንኳን ለዒድ አል ፈጥር በዓል አደረሳችሁ፤ ከረመዳን ወር ጾም በኋላ የሚመጣው ዒድ አል ፈጥር፣ የአንድነትና የበጎነት በዓል ነው ብለዋል፡፡

በረመዳን ጊዜ ጾሙም፣ ሶላቱም ሆነ ኢፍጣሩ በአንድነት የሚደረግ ነው፤ ይህም አብሮነትን ያጠናክራል ብለዋል በመልዕክታቸው፡፡

በሌላ በኩል በጾሙ እና በበዓሉ ጊዜ ድኾችን ረስቶ፣ ዐቅመ ደካሞችን ትቶ ማፍጠር አይፈቀድም ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በጎ ማድረግ ዋናው የረመዳንም ሆነ የዒድ ዕሴት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የዒድ አል ፈጥር ዕሴቶች ለሀገር ግንባታ አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሀገር ያለ አብሮነት እና ያለ በጎነት ልትገነባ አትችልም ነው ያሉት፡፡

ኅብረ-ብሔራዊነትን ጌጥና ውበት የሚያደርገው አብሮነት ነው፤ ብዝኃነትን ዕድልና ጸጋ የሚያደርገውም አብሮነት ነው ብለዋል።

አብሮነት ዘላቂ የሚሆነው ደግሞ በበጎነት ዕሴት ላይ ከተገነባ ነው ብለዋል አቶ ተመስገን ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፡፡

በጎነት የራስን ለሌላው መተው ነው፤ የሌላውን ሕመም መካፈል ነው፤ ለሌላው በደል ዕውቅና መስጠት ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡

በእነዚህ ጠቃሚ ዕሴቶች ሀገርን እየገነባን በዓሉን እንደምናከብር ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.