ርዕሳነ መሥተዳድሮች ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የተለያዩ ክልሎች ርዕሳነ መሥተዳድሮች 1 ሺህ 446ኛውን የዒድ አልፈጥር በዓል አስመልክተው ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ዒድ አል ፈጥር የምሥጋና እና የበጎ አድራጎት በዓል ስለሆነ ለአቅም ደካማ ወገኖች መልካም ነገርን በማድረግ በዓሉን ማሳለፍ ይገባል ብለዋል፡፡
ሕዝበ ሙስሊሙ በረመዳን ወር ያሳውን አንድነት፣ መተዛዘን፣ መደጋገፍና ለሰላም ሲያደርጋቸው የነበሩ ጸሎቶችን በሌሎች ጊዜያትም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሀመድ በበኩላቸው፤ ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች እንኳን ለዒድ አልፈጥር በዓል በሰላም አደረሳችሁ በማለት መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
በተመሳሳይ የድሬዳዋ አሥተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መልዕክት፤ ረመዷንን በጾም እና በፀሎት ያሳለፍን ሁሉ የተቸገሩ ወገኖችን በማሰብ የዒድ አልፈጥር በዓልን በደስታ ልናሳልፍ ይገባል ብለዋል፡፡
እንዲሁም የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ባስተላለፉት መልዕክት በረመዳን ወር አቅመ ደካማ የሆኑትን በመደገፍ ቅዱስ የሆነውን ኃይማኖታዊ ስርዓት ፈፅማችሁችኋልና ለዒድ አልፈጥር በዓል እንኳን በሰላም አደረሳችሁ ብለዋል፡፡