የብልጽግና ፓርቲ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ኃላፊዎች ለዒድ አልፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 20፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብልጽግና ፓርቲ የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ኃላፊዎች 1 ሺህ 446ኛውን የዒድ አልፈጥር በዓል አስመልክተው ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በፓርቲው የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ ባስተላለፉት የመልካም ምኞት መግለጫ መልዕክት፤ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ዘንድ ረመዳን ታላቅ ወር መሆኑን አንስተው፤ እርስ በርስ መረዳዳት፣ ተካፍሎ መብላትና መተዛዘን የሚንጸባረቅበት መሆኑን ገልጸዋል።
በረመዳን ወር የሚታየውን መረዳዳት፣ እዝነት እና አንድነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የፓርቲው የአማራ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ይርጋ ሲሳይ በበኩላቸው፤ ሕዝበ ሙስሊሙ ታላቁን የዒድ አልፈጥር በዓል ሲያከብር ለሌሎች የማሰብን በጎ ተግባር ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
በሌሎች ደስታ ውስጥ የራስን ደስታ ማግኘት መሆኑን በተግባር ያሳየው ሕዝበ ሙስሊሙ፤ በዓሉን ሲያከብር መልካም የመሥራትን፣ ለሌሎች የማሰብን በጎ ተግባር ሊያጠናክር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ለአንድነት በመትጋት እና የሰላምን ዋጋ ከፍ በማድረግ ለቀጣይ ትውልድ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማስረከብ ኃላፊነትን መወጣት እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር ) በዓሉ ለመላው ለእስልምና እምነት ተከታዮች የሰላም የፍቅርና የአንድነት እንዲሆን ተመኝተዋል።
በዓሉን ስናከብር በመረዳዳት እና የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ፣ ደጋፊ ካጡ ወገኖቻችን ጎን በመቆም ሊሆን ይገባል ብለዋል በመልዕክታቸው።