ከንቲባ አዳነች የዒድ አል ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ አጋሩ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ 1 ሺህ 446ኛውን የዒድ አል ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ማዕድ አጋርተዋል።
ከንቲባ አዳነች በቦሌ ክ/ከተማ ተስፋ ብርሃን ቁጥር 2 የምገባ ማዕከል በመገኘት ነው የዒድ አል ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ማዕድ ያጋሩት፡፡
ከንቲባዋ በዚህ ወቅት በዓሉን በመደጋገፍና በመተጋገዝ ማሳለፍ እንደሚገባ ገልጸው÷ የኢትዮጵያውያንን የመጠያየቅና የመደጋገፍ እሴት ይበልጥ ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ በስሩ በሚገኙ ሀሉም ክፍለ ከተሞች ለእምነቱ ተከታዮችና በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች ማዕድ ማጋራቱን አንስተዋል።
በረመዳን ወቅት በከተማዋ በሚገኙ 24 የምገባ ማዕከላት የኢፍጣር መርሐ ግብር ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።
በታምራት ደለሊ