አረንጓዴ አሻራ ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካት ትልቅ አቅም መፍጠሩ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ለዘላቂ የልማት ግቦች መሳካትና ለአካባቢ ጥበቃ ትልቅ አቅም እየፈጠረ እንደሚገኝ የአረንጓዴ አሻራ ብሔራዊ የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) ገለጹ።
አደፍርስ ወርቁ (ዶ/ር) እንዳሉት÷የአረንጓዴ አሻራ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የተጎዱ መሬቶች እንዲያገግሙ ለማድረግ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም ኢኮኖሚ ለመገንባት ታቅዶ እየተከናወነ የሚገኝ መርሐ ግብር ነው፡፡
መርሐ ግብሩ ነባር ደኖችና የውሃ ሀብቶች የሚጠበቁበት እንዲሁም ግድቦች በደለል እንዳይሞሉ የሚያደርግና ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡
በከፍተኛ የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የማህበረሰብ ተሳትፎ እየተተገበረ የሚገኘው አረንጓዴ አሻራ ÷ሁሉም ዜጋ ለአካባቢ ጥበቃ በአዲስ ዕይታ እንዲነሳ ማድረጉንም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖ ተጋላጭ መሆኗን የጠቀሱት አስተባባሪው÷መርሐ ግብሩ ይህን ተጋላጭነት እንዲቀንስ እና የመቋቋም አቅም እንዲጨምር እንዲሁም ዘላቂ ልማትን ማሳካት ማስቻሉን አስረድተዋል።
አረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ስም በዓለም አደባባይ በመልካም እንዲነሳ ያደረገ መሆኑን ገልጸው÷በርካታ ሀገራትም ከኢትዮጵያ ልምድ ለመቅሰም እየጠየቁ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወደ ካርበን ገበያ እየገባች እንደምትገኝና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርም በገበያው ውስጥ በቀዳሚነት እንድትጠቀም የሚያስችላት መሆኑን ነው ያመላክቱት፡፡
መርሐ ግብሩ የኢኮኖሚ ውጤቶችን እያስመዘገበ እንደሚገኝ መግለጻቸውንም የዘገበው ኢዜአ ነው፡፡