የወንድማማችነት እሴትን በማጠናከር ለሀገር ሰላምና እድገት በጋራ መስራት ይገባል -የዒድ አልፈጥር በዓል ተሳታፊዎች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 21፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴትን በማጠናከር ለሀገር ሰላምና እድገት በጋራ መስራት እንደሚገባ የአዲስ አበባ የዒድ አል ፈጥር በዓል ተሳታፊዎች ገለጹ።
1 ሺህ 446ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የሶላት ሥነ-ሥርዓት በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ስታዲየም ተካሂዷል።
የበዓሉ ተሳታፊዎች የረመዳን ጾም አብሮነትንና በጎነትን በሚያጠናክሩ ተግባራት ማሳለፍቸውን ገልፀው÷ እነዚህን መልካም እሴቶች ሁልጊዜም መተግበር እንደሚገባ የሚያስተምር መሆኑን ተናግረዋል።
የአብሮነትና የወንድማማችነት እሴትን በማጠናከር ለሀገር ሰላምና እድገት መስራት እንደሚገባም ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የገለጹት።
ከበዓሉ ተሳታፊዎች መካከል ሁሴን በሽር መሐመድ እንዳሉት÷ የአብሮነትና የወንድማማችነትት እሴትን በማጎልበት ለሀገር እድገት መስራት የሁሉም ሀላፊነት ነው።
የህብረተሰቡን የቆየ የአንድነት እና አብሮነት እሴት አጠናክሮ በማስቀጠል ለሀገር እድገት በጋራ መረባረብ ይገባል ብለዋል።
ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በሀገር ጉዳይ ላይ ህብረቱንና አንድነቱን ማጠናከር እንዳለበት የተናገሩት የበዓሉ ተሳታፊ ደግሞ ሳዲቅ ንጋኘው ናቸው።
ሰላም ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገት ያለው ፋይዳ የላቀ በመሆኑ ለሀገር ዘላቂ ሰላም ግንባታ ሁሉም ዜጋ የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ተናግረዋል።
ብዝሃነታችንን እንደ ፀጋ በመጠቀም ለሀገር ግንባታ ማዋል ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የበዓሉ ተሳታፊ መንሱር ጀማል ናቸው።
ብዝሃነታችን እንደ ልዩ ጸጋ እና አቅም በመጠቀም ለኢትዮጵያ እድገት እና ከፍታ መስራት ከሁላችንም ይጠበቃል ብለዋል።