ዴንማርክ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ዴንማርክ ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የምታደርገውን ጥረት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኗን በኢትዮጵያ የዴንማርክ አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሩፕ ገለጹ።
አምባሳደር ሱኔ ክሮግስትሩፕ በተለይ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን አጋርነት አጠናክራ ለመቀጠል እና በተለያዩ ዘርፎች በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ ናት።
ሀገሪቱ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ እድገት ለመደገፍ አዲስ ሀገር አቀፍ ፕሮጀክት በቅርቡ ይፋ እንደምታደርግ ገልጸው÷ ኢትዮጵያ እያካሄደች ካለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ጋር የሚጣጣም እንደሆነም አመላክተዋል።
የዴንማርክ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የስራ እድል ፈጠራ እና ኢኮኖሚ ልማት ውስጥ ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ስለመሆናቸውም አንስተዋል።
ዴንማርክ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁለትዮሽ ግንኙነት በማሳደግ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በልማት ላይ ትኩረት ሰጥታ ትብብሯን እንደምታጠናክርም ነው አምባሳደር ሱኔ የገለጹት።
በመሳፍንት ብርሌ