በኢቢኤስ የተላለፈው የሀሰት መረጃ በሀገሪቱ ግጭት ለማስፋፋት ያለመ መሆኑ ተነገረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሰሞኑ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ብርቱካን ተመስገን በተባለች ግለሰብ ዙሪያ የተሰራው የተቀነባበረ የሀሰት ዘገባ ግጭት ለማስፋፋት ያለመ መሆኑን መገንዘባቸውን ፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ያነጋገራቸው የሐረር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ሀሳባቸውን ከሰጡ የከተማው ነዋሪዎች መካከል ወጣት ሙራድ አብዲ የቀረበው የሀሰት ዘጋቢ ፊልም ህዝብን በሀሰት መረጃ ለማሳሳት እየተሰራ እንደሆነ የሚያሳይ መሆኑን ገልጿል።
እንዲህ አይነት ድርጊት ሀገርን የሚጎዳ በመሆኑ የሚያሳዝንና ተቀባይነት የሌለው ነው ብሏል።
ይህም በህዝቦች መካከል እንዲሁም በህዝብና መንግስት መካከል መጠራጠርን ለመፍጠር መሆኑን ጠቅሶ፤ ይህም በዋናነት በሀገሪቱ ግጭት በማስፋፋት የፖለቲካ ፍላጎት ለማሳካት የተወጠነ መሆኑን ተናግሯል።
የህግ ባለሙያው ጠበቃ አብዲ አደም በበኩላቸው በኢቢኤስ ቴሌቪዥን ላይ ሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልሙ ድብቅ ፍላጎት ባላቸው አካላት የተቀናበረ መሆኑ መጋለጡን ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ የሚሰራጩ መረጃዎችን በአግባቡ መመርመር እንዳለበት ያሳየ ስለመሆኑ ገልጸዋል።
ዜጎችን ለፖለቲካ ፍላጎት አላማ ማሳኪያ አድርጎ መንቀሳቀስ ተቀባይነት እንደሌለውም አመልክተዋል።
ሌላው የከተማው ነዋሪ አሸናፊ ሰለሞን እንደተናገሩት፤ የሀሰት ዘገባ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረና እየሰፋ መጥቷል።
ይህ በብርቱካን ተመስገን ዙሪያ የተሰራው ሀሰተኛ ዘጋቢ ፊልም አንዱ ማሳያ መሆኑን አንስቶ፤ ህብረተሰቡ መረጃዎችን በአግባቡ መመርመርና መፈተሽ እንዳለበት ያስተማረ መሆኑን ተናግሯል።
በተስፋዬ ኃይሉ