ሹዋሊድ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የዘንድሮው የሹዋሊድ በዓል ሰላምን እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ እንዲከበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሐረሪ ክልል አስታወቀ፡፡
አከባበሩን አስመልክቶ የክልሉ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ እንዳለው፤ በዓሉ “የቅርስ ሃብቶቻችን ለቱሪዝም ልማታችን” በሚል መሪ ሐሳብ በቅርቡ ይከበራል፡፡
ሹዋሊድ ከበዓልነቱ ባሻገር ለሐረሪ ሕዝብ ጥልቅ የሆነ ማኅበራዊና ምጣኔ ሃብታዊ ዕሴቶች መገለጫ ነው ተብሏል።
የቱሪዝም ዘርፉ እንዲጎለብት ከማድረግ አንፃርም የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱን መግለጫው አመላክቷል፡፡
የዘንድሮው የሹዋሊድ በዓል አከባበርም ሰላምን፣ አብሮነትን እና ኅብረ-ብሔራዊ አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ እንዲሆን አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሹዋሊድ በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሣይንስ እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ ዓለም አቀፍ ቅርስ ሆኖ መመዝገቡ ይታወቃል፡፡