Fana: At a Speed of Life!

ለውጡን ተከትሎ በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ ናቸው – ግርማ አመንቴ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶች ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገሩ መሆናቸውን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለፁ።

ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በግብርና ዘርፍ የተመዘገቡ ስኬቶችን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ÷ በዘርፉ መዋቅራዊ ሽግግርን ማምጣት የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በተለይ የኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴንና የሜካናይዜሽን እርሻን የማስፋት እንዲሁም በዝናብ ላይ ጥገኛ የነበረውን ግብርና በመቀየር ዓመቱን ሙሉ ወደ ማረስ በመገባቱ ምርማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሻገረ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የተመዘገበውን ስኬት ዘላቂ ለማድረግ በአረንጓዴ አሻራ መርሃሐ ግብር አማካኝነት ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የግብርና ልማት ለመተግበር እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ መለስ መኮንን(ዶ/ር) በበኩላቸው÷ ከለውጡ በፊት በመኸር 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት ይታረስ እንደነበር አስታውሰው÷ አሁን ላይ ወደ 20 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር ማሳደግ ተችሏል ነው ያሉት።

በዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚሰበሰበውን ምርት ከ293 ሚሊየን ኩንታል ወደ 608 ሚሊየን ኩንታል ምርት ከፍ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል።

ከለውጡ ወዲህ ባሉት ዓመታት የስንዴ ምርታማነትን በማሳደግ ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል በተጀመረው ኢኒሼቲቭ ከፍተኛ ውጤት መገኘቱን ገልጸዋል።

በመኸር ብቻ የሚገኘው ዓመታዊ የስንዴ ምርት ከ48 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ወደ 152 ሚሊየን ኩንታል ከፍ ማለቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በ2011 ዓ.ም በ3 ሺህ 500 ሄክታር መሬት የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ደግሞ አሁን ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር ማደጉን ገልጸው÷ ከዚህም 172 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ እየተገኘ ያለው ስኬት የአደጋ ስጋትን በራስ አቅም ለመቋቋም የተጀመረውን ስራ እያገዘ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) ናቸው።

ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመቻል ፖሊሲ ተቀርፆ በሁሉም ክልሎች ወደ ስራ መገባቱንም ገልጸዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.