በ18 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ግንባታው እንዲጠናቀቅ ውል የተገባለት ስታዲየም
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የብሔራዊ ስታዲየም ምዕራፍ ሁለት ሎት ሁለትና ሦሥት የማጠቃለያ ግንባታ በ18 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር እንዲከናወን የሚያስችል ውል ተገብቷል፡፡
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ እንዳሉት፤ ከለውጡ ወዲህ የተገነቡና የታደሱ 10 ሺህ 494 መካከለኛ እና አነስተኛ የስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች በየትምህርት ቤቶቹና በየመንደሩ አሉ፡፡
አሁን ደግሞ የብሔራዊ ስታዲየም ምዕራፍ ሁለት ሎት ሁለትና ሦሥት የማጠቃለያ ግንባታ በ18 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር፤ በ18 ወራት አጠናቅቆ ለማስረከብ በወጣው ዓለም አቀፍ ጨረታ አሸናፊ ከሆነው ከቻይናው ኮሙኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ጋር ውል ተፈራርመናል ብለዋል።
የኤም ኤች አማካሪ መሰለ ኃይሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የምዕራፍ ሁለት ሎት ሁለትና ሦሥት ስምምነት የፊፋን ደረጃ የጠበቁ የጣራ፣ የቴክኖሎጂና የማስዋብ ውሎችን ማካተቱን አብራርተዋል፡፡
በዚሁ መሠረት በትንሹ 1 ሺህ 200 መጸዳጃ ቤቶች፣ 800 የእጅ መታጠቢያዎች፣ ሙሉ የሜዳ ሥራ፣ የጣራና የቴክኖሎጂ ሥራዎችን ያካትታል ነው ያሉት፡፡
ሥራው በ18 ወራት ሲጠናቀቅም ስታዲየሙ አኅጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ማስተናገድ እንደሚችል ማረጋገጣቸውን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
ይህንን የስታዲየም ግንባታ ስምምነት በደስታና በፍላጎት ተቀብለናል፤ በተቀመጠው ስምምነት መሠረት በጥራትና በፍጥነት በተቀመጠለት ጊዜ ሠርተን እናስረክባለን ያሉት ደግሞ የቻይናው ኮሙኒኬሽንስ ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ማኔጀር ሲን ናቸው፡፡