የአቪዬሽን ደኅንነት በሚጠናከርበት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔዎች ተላለፉ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአቪዬሽን ደኅንነት ተጠናክሮ በሚቀጥልበት ስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ውሳኔዎች መተላለፋቸውን የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት አስታውቋል፡፡
አገልግሎት ለፋና ዲጂታል እንደገለጸው÷ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ በወቅታዊ ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና በኢንዱስትሪው ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በቀረበው ጥናት ላይ ትናንት ውይይት አድርጓል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ም/ዳይሬክተር ጀነራልና የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሲሳይ ቶላ በዚህ ወቅት÷የኢትዮጵያ የአቪዬሽን ደኅንነት በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ተቋማት መስፈርት መሰረት አስተማማኝና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑ በርካታ ማረጋገጫዎች እየተሰጡ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ዘርፉ ውጤታማ ጉዞ እያደረገ ቢሆነም ከአቪዬሽን ደኅንነት ልዩ ባህሪና ውስብስብነት በመነሳት ሀገራዊ እና ቀጣናዊ የጸጥታ ሁኔታው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በተለይም በብሔራዊ አየር መንገድ ተወዳዳሪነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ጥንቃቄ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሠራርን በማጠናከር እና በስትራቴጂክ ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረት በማድረግ ነቅተው በጋራ መሥራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
መድረኩ የዘርፉን ስጋቶች፣ ክፍተቶችና ተጋላጭነቶች በመገምገም እየተወሰዱ የሚገኙ የደኅንነት ርምጃዎች እንዲሁም ዓለም አቀፍ አሠራርንና ስታንዳርድን በመጠበቅ ኢትዮጵያን ከፍ የሚያደርግ አገልግሎት መስጠት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በስፋት የተመከረበትና ውሳኔ የተላለፈበት መሆኑ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ የተሳተፉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሲቪል አቪዬሽን ሴኪዩሪቲ ኮሚቴ አባላት በበኩላቸው÷ በቀጣይ የአቪዬሽን ኢንዱስትሪው የደረሰበትን የዕድገት ደረጃ አስጠብቆ ለመሄድ በየተቋማቱ የሚገኘውን አቅም አቀናጅቶ የመጠቀም ሥራው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
የአቪዬሽን ደኅንነቱ የተረጋገጠና አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል ውስጣዊና ውጫዊ ስጋቶችን እንዲሁም ሀገራዊና ቀጣናዊ ሁኔታዎችን በተመንተን ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ወቅታዊ ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
የኢትዮጵያንና የአፍሪካዊያን ሁሉ ኩራት የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚደረገው የጋራ ርብርብ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡
በቀጣይ ዓለም ከደረሰበት ዕድገት አንጻር ኢንዱስትሪው የሚመራበት ሮድማፕ እንዲዘጋጅ እንዲሁም ወቅታዊ የኢንዱስትሪው ሁኔታ በየጊዜው እየተገመገመ እንዲመራ አቅጣጫ መቀመጡም ተመላክቷል፡፡