Fana: At a Speed of Life!

ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከተረጂነት ለማላቀቅ የሚያስችሉ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግቧል – አቶ አደም ፋራህ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ ኢትዮጵያን ከተረጂነት በማላቀቅ ወደ ተሟላ ሉዓላዊነት ለማሸጋገር የሚያስችሉ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊና የብልጽግና ፓርቲ ም/ፕሬዚዳንት አደም ፋራህ ገለጹ።

አቶ አደም ፋራህ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተገኙ ስኬቶች እና የወደፊት ትኩረት አቅጣጫዎች ዙሪያ በሰጡት ማብራሪያ÷ሕዝብ ሲያነሳቸው የነበሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስብራቶች ለውጡ እንዲመጣ ያደረጉ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን አብራርተዋል።

በብልጽግና ፓርቲ መሪነት የለውጡ መንግስት የኢትዮጵያን ታሪካዊና አሁናዊ ችግሮች በመለየት ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት በቂ ትንተና አድርጎ ወደ ሥራ መግባቱን አስረድተዋል፡፡

በተለይ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር ፓርቲው በግንባር አርአያ በመሆን ጭምር በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል ነው ያሉት፡፡

ለአብነትም በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ በአብላጫ ድምጽ አሸንፎ መንግስት የመመስረት ህገ-መንግስታዊ መብት ቢያገኝም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በተለያዩ የአመራር ደረጃዎች ላይ ማሳተፉን አስታውሰዋል።

ይህም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አዲስ ምእራፍ የከፈተ መሆኑን ነው አቶ አደም አጽንኦት የሰጡት፡፡

ኢትዮጵያ በብልጽግና ፓርቲ መሪነት ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዴሞክራሲ ተቋማትን በማጠናከር፣ ማህበራዊ ልማትን በማጎልበት፣ ለጎረቤት ሀገራት ቅድሚያ የሰጠና ትብብር ላይ የተመሰረተ ዲፕሎማሲን ተግባራዊ በማድረግ ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ መቻሏን ተናግረዋል።

ከልመናና ተረጂነት በመላቀቅ የተሟላ ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ይገባል በሚል መርህም ተስፋ ሰጪ የኢኮኖሚ ልማት ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል ብልጽግና ፓርቲ ለማህበራዊ ልዕልና፣ ለተረጋጋ የፖለቲካ ስርዓት እንዲሁም ቅቡልነት ያለው ሀገረ መንግስት ለመገንባት ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራቱን ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም ፓርቲው ለሰላማዊ መፍትሄ ያለውን ቁርጠኝነት በተደጋጋሚ በተግባር ማረጋገጡን ጠቅሰው÷ የፕሪቶሪያውን ስምምነት በማሳያነት አንስተዋል፡፡

በአፍሪካ ግዙፍ ፓርቲ የሆነው የብልጽግና ፓርቲ ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካዊ እና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችን በማጠናከር ለፍትሃዊ እና የጋራ ተጠቃሚነት እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በቀጣይም ፓርቲው መሰል አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው አቶ አደም ፋራህ ያረጋገጡት፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.