Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መደበኛና ተከታታይ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሊያወጣ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንቱ መደበኛና ተከታታይ የውጭ ምንዛሪ ጨረታ ሊያወጣ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ÷ ብሔራዊ ባንክ በየሁለት ሳምንት መደበኛ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታ ማካሄድ እንደሚጀምር ገልጿል፡፡

ጨረታዎቹም ለሚቀጥሉት በርካታ ወራት እንደሚካሄዱ ያመላከተ ሲሆን÷ዓላማውም የማዕከላዊ ባንኩን የተረጋጋ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ግብን ለማሳካት ነው ብሏል፡፡

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ከተጀመረ ወዲህ የወጪ ንግድ በመስፋፋቱ፣ የውጭ ሐዋላ በመጨመሩና የካፒታል ፍሰት በማደጉ ምክንያት የኢትዮጵያ የውጭ ክፍያ ሚዛን በከፍተኛ ደረጃ የመሻሻል አዝማሚያማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡

የማዕከላዊ ባንኩ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት በታሪኩ ከፍተኛው መሆኑን የጠቀሰው መግለጫው÷ በሀገሪቱ ውስጥ ብቸኛው የወርቅ ገዢ ለሆነው ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የቀረበው የወርቅ መጠን ከፍተኛ መሆን የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ መጠባበቂያ ክምችት ከተገመተው በላይ እንዲጨምር ማድረጉን አንስቷል፡፡

ከዚህ ከተጠበቀው በላይ ከሆነው የውጭ ምንዛሪ ግኝት አንጻር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቀጣይ ወራት በመደበኛነት በየሁለት ሳምንቱ የውጭ ምንዛሪ ሽያጭ ጨረታዎችን ለማካሄድመወሰኑን ነው የተገለጸው፡፡

ይህ አካሄድ በማዕካላዊ ባንክ እየተከማቸ ካለው የውጭ ምንዛሪ የተወሰነውን መጠን ለግሉ ዘርፍለማቅረብና የማዕከላዊ ባንኩን የገንዘብ ፖሊሲ ዓላማ ለማሳካት እንደሚያግዝ ተመላክቷል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ጨረታው የውጭ ምንዛሪ ገበያን ለማረጋጋትና ሪፎርሙ ከተጀመረ ወዲህ መሻሻል እያሳየ የመጣውን የውጭ ክፍያ ሚዛን በይበልጥ ለማጠናከር እንደሚረዳ ታምኖበታል ተብሏል፡፡

በመሆኑም ፍላጎቱ ያላቸው ባንኮች በተሰጠው የጊዜ ሰሌዳና በተቀመጠው አካሂድ መሰረት የጨረታ ሰነዶቻቸውን እንዲያስገቡ ባንኩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ለጨረታ የቀረበው የውጭ ምንዛሪ መጠን 50 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ሲሆን÷ ጨረታው ማክሰኞ መጋቢት 23 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚካሄድ ተመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.