የቻይና የልማት ፈንድ በኢትዮጵያ አዲስ በሚገነባው አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት መሳተፍ እንደሚፈልግ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የቻይና-አፍሪካ የልማት ፈንድ በኢትዮጵያ አዲስ በሚገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለው የተቋሙ ምክትል ፕሬዚዳንት ዩ ዡሮይ ገለጹ።
በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር ተፈራ ደርበው ከምክትል ፕሬዚዳንቱ ጋር በሁለቱ ሀገራት የትብብር መስኮች ዙሪያ ተወያይተዋል።
አምባሳደር ተፈራ ደርበው በዚሁ ወቅት፤ የሀገራቱን ትብብር ማጠናከርና ኢንቨስትመንትን ማሳደግ እንደሚገባ መግለጻቸውን በቻይና የኢትዮጵያኤምባሲ መረጃ አመላክቷል፡፡
በኢትዮጵያ አዲስ የሚገነባውን ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጨምሮ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስና ኢትዮ-ቴሌኮምን በተመለከተ ገለጻ አድርገዋል።
ዩ ዡሮይ በበኩላቸው፤ ውይይቱ የሀገራቱን የልማት ትብብር ለማሳደግና አዳዲስ የትብብር መስኮችን ለመፍጠር እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡
ተቋማቸው በኢትዮጵያ አዲስ በሚገነባው የአውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳለውም አረጋግጠዋል፡፡