ከሆርቲካልቸር ዘርፍ 366 ሚሊየን ዶላር ተገኘ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ባለፉት ሥምንት ወራት ከሆርቲካልቸር ዘርፍ 366 ሚሊየን ዶላር መገኘቱን የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
“ሆርቲካልቸር ለዘላቂ ሀገራዊ ግብ” በሚል መሪ ሐሳብ ዓለም አቀፍ የሆርቲካልቸር ዐውደ-ርዕይ በሚሊንየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር እንደ ሀገር በዘርፉ እምቅ አቅም መኖሩን ገልጸው፤ ይህን አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል መንግሥት ልዩ የትኩረት አቅጣጫ አስቀምጦ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡
መንግሥት የሆርቲካልቸር ዘርፉን ከሚያንቀሳቅሱ አካላት ጋር የጠበቀ ቁርኝት እንዳለው አንስተው፤ በቀጣይ የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ዘርፉን ከዚህ በላይ የማሳደግ ሥራ እንደሚራ አረጋግጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሆርቲ ካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ሊቀመንበር ነጋ መኳንንት በበኩላቸው፤ የሆርቲ ካልቸር ዘርፉ በሀገር ሁለንተናዊ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚያደርገው ድጋፍ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
በተጨማሪም ከፍተኛ የሰው ኃይልን በውስጡ በመያዝ የሥራ ዕድል እጥረትንም እየቀረፈ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የዘርፉን ተደራሽነት ለማስፋትም መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መሥራትና ባለሀብቶችን የማሳተፍ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚጠበቅበት አመላክተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር በተዘጋጀው ዐውደ-ርዕይ ላይ በርካታ ባለሀብቶችና የውጭ ሀገራት ዲፕሎማቶች እየተሳተፉ ነው፡፡
አሸብር ካሳሁን