የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገት ለማስቀጠል የትራንስፖርት ዘርፉ ወሳኝ ሚና መጫወት አለበት – ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እድገትና የብልጽግና ጉዞ ለማስቀጠል የትራንስፖርት ዘርፉ አስቻይ የሆነ ወሳኝ ሚና መጫወት እንዳለበት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ያለውን የትራንስፖርት ችግር የሚያቃልሉ 100 ዘመናዊ የኤሌክትሪክ አውቶቡሶችን በመንግስት እና በግል አጋርነት ወደ አገልግሎት አስገብቷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)÷ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት አገልግሎትን በማቀላጠፍ አርዓያነት ያለውን ተግባር እያከናወነ መሆኑን አመላክተዋል።
በትራንስፖርት ምክንያት በመንገድ ላይ የሚጠፋ ጊዜ ማጠር እንዳለበት እና ከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ ያለውን ችግር በዘላቂነት ለመቅረፍ በርካታ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝም አንስተዋል።
በዚህም መንገዶች እየሰፉ፣ የእግረኛ እና የተሽከርካሪ መንገዶች እየተለዩ፣ አዳዲስ መንገዶች እየተገነቡ እንዲሁም ለሕብረተሰቡ የትራንስፖርት አማራጮች እየቀረቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ተስማሚ የሆኑና ያለንን ታዳሽ ኃይል የሚጠቀሙ ተሽከርካሪዎችን ወደ ስራ ለማስገባት በወጣው ፖሊሲ መሠረት ዛሬ ወደ ስራ የገቡት አውቶቡሶች ይህንን ለመፈጸም አይነተኛ ማሳያ ናቸው ማለታቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመለክታል።