Fana: At a Speed of Life!

የሰብል መውቂያና መፈልፈያ የሠሩ …

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ታምራት ዓለሙ የሠሩት ማሽን የተለያዩ ሰብሎችን ለመውቃትና ለመፈልፈል የሚውል ነው።

ማሽኑ የአገዳ እና ብርዕ ሰብሎችን በአግባቡ ለመውቃት እንደሚያገለግል ታምራት ዓለሙ ገልጸዋል፡፡

ማሽኑ ወጪ ቆጣቢ እና ችግር ፈቺ ከመሆኑም ባሻገር አነስተኛ ማሳ ላላቸው አርሶ አደሮች አገልግሎት እንደሚሰጥም ተናግረዋል፡፡

አነስተኛ ምርት በትንሽ ማሳ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ከውጪ ማሽን ማስገባት ስለማይችሉ እስከ አሁን በእጅ እና በእንስሳት ሲወቁ እንደነበር አውስተው፤ ይህ ማሽን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚረዳቸው አቶ ታምራት አረጋግጠዋል፡፡

ማሽኑ እራሱ ከመውቃቱ በተጨማሪ የራሱ ወንፊት እንዳለው ጠቁመው፤ በቆሎ፣ ጤፍ፣ ሩዝ፣ ስንዴ፣ ገብስን ጨምሮ ለሌሎች ሳራማ እና አገዳማ ሰብሎችን ለመውቃት እንደሚጊሊግል አስረድተዋል፡፡

ሰብሎቹን በመውቃት ሂደቱም ገለባ፣ እብቅ እና አላስፈላጊ ብናኝ ነገሮችን ከምርት በመለየት ለወፍጮ ቤት በቀጥታ የሚውል የጠራ ምርትን ያስገኛል ነው ያሉት፡፡

ከዚህ ባሻገር ማሽኑ በዲናሞ እንዲሁም በጄኔሬተር መሥራት የሚችል መሆኑን በመግለጽ፤ ተፈትቶ ወይም እንዳላ በቀላሉ ከቦታ ቦታ ማንቀሳቀስ ይቻላል ነው ያሉት፡፡

ይህ ማሽን ለአርሶ አደሩ ብሎም ለመላው ሀገሪቱ እና ለአፍሪካ ጠቃሚ መሆኑንም አስገንዝቧል፡፡

ይህን ማሽን በማከራየት እና በመሸጥ ወደ ገበያው በስፋት ለመግባት ማሰባቸውን ጠቁመው፤ ሙሉ ዋስትና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በአቤል ንዋይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.