Fana: At a Speed of Life!

የለውጡ ዓመታት በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው – አቶ ከፍያለው ተፈራ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መጋቢት 24 ሀገራችንን ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረ ታሪካዊ ቀን ነው ሲሉ በብልጽግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ከፍያለው ተፈራ ገለጹ።

አቶ ከፍያለው ተፈራ መጋቢት 24ን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ÷ ያለፉት የለውጡ ዓመታት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ስኬት የተመዘገቡበት እንደሆነ ገልጸዋል።

መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም በሀገሪቱ የመጣው የለውጡ መንግሥት ለዘመናት የቆዩ የኢኮኖሚ፣ ዴሞክራሲና የማንነት ጥያቄዎች ትክክለኛ አቅጣጫ እንዲይዙ በማድረግ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሸጋገር ማስቻሉን አመላክተዋል።

ነባሩን የፖለቲካ ባህል ለመቀየር በተደረገው ጥረት ነፃና አሳታፊ ምርጫ በማካሄድ፣ የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትን በማረጋገጥና ከፖለቲካ ተጽእኖ የፀዱ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት የህዝቡን ተቀባይነት ያሳደገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

የለውጡ መንግሥት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን በማድረግ ሀገሪቱን ከልመና በማውጣት፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የወጪ ንግድን በማሳደግ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንድትሻገር አድርጓታልም ነው ያሉት።

የሀገሪቱ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የትግል ውጤት የሆነው መጋቢት 24÷ ኢትዮጵያን ከመበታተን ፍራቻ ታድጎ ነፃነት ማስገኘቱንም ተናግረዋል።

የመደመር እሳቤን ወደ ተግባር በመቀየርም የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በፍትህ፣ በጸጥታ እና ሌሎች ተቋማት ላይ ሪፎርሞችን በማካሄድ ማህበረሰቡ ግልጽ እና ነጻ የሆነ አገልግሎት እንዲያገኝ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ በሁሉም ዘርፍ ለተመዘገቡ ስኬቶች መሰረት በመሆኑ ላደረገው ተሳትፎና ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት አቶ ከፍያለው÷ የተገኙ ድሎች እንደሚቀጥሉ እና ኢትዮጵያ በ2043 የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት እንድትሆን ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።

በጸሐይ ጉልማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.