Fana: At a Speed of Life!

በሀገራዊ የለውጥ ጉዞው መልካም አሥተዳደርን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች ስኬት መመዝገቡ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በጀመረችው ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሰላም፣ ልማትና በመልካም አሥተዳደር ዘርፎች ስኬታማ ሥራዎች መከናወናቸው ተገለጸ፡፡

የብልጽግና ፓርቲ ምክር ቤት አባልና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኢሳቅ አብዱልቃድር እንዳሉት፤ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ በርካታ ሀገራዊና ክልላዊ የልማት ፕሮጀክቶች በስኬት በመጠናቀቅ ላይ ናቸው፡፡

በዚህም በክልሉ የተከናወኑ ተግባራት የሕዝቡን ሁሉን አቀፍ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ያስቻሉ መሆናቸውን አንስተው፤ በሰው ተኮር ሥራዎችም ስኬታማ መሆን ተችሏል ብለዋል፡፡

የሌማት ትሩፋት፣ የስንዴ ኢኒሼቲቭ፣ የአረንጓዴ ልማት፣ የከተማ ልማት የመሳሰሉ ሀገራዊ ኢንሼቲቮችን ከማስፈጸም አንጻር ሕብረተሰቡን በማስተባበር ውጤታማ ሥራ መሠራቱንም አብራርተዋል፡፡

አሶሳ ከተማን ውብ፣ ጽዱና ለኑሮ ተስማሚ የማድረግ ሥራ የተሻለ አፈጻጸም እየተመዘገበበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ታዳጊ ክልሎች አጋር ሲባሉ መቆየታቸውን አውስተው፤ በለውጡ ማግሥት እነዚህ ክልሎች በሀገራቸው ጉዳይ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሆኑበት ዕድል መፈጠሩን አንስተዋል።

በክልሉ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዲሰፋ በተደረገው ጥረትም፤ ከዘጠኝ በላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተሻለ ዴሞክራሲያዊ ተሳትፎ የሕዝብ ውክልናቸውን በተግባር ለማሳየት ጥረት ያደረጉበት ምቹ ሁኔታ እንደነበር ተናግረዋል።

በተለያዩ ዘርፎች የተከናወኑ ስኬታማ ሥራዎችን በማጠናከር የሀገሪቱን ሁሉን አቀፍ ብልጽግና ዕውን ለማድረግ መሥራት እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.