Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ በትምህርት ዘርፍ ትብብራቸውን ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ)ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ በቀጣይ በሚኖራቸው ግንኙነቶች በትምህርቱ ዘርፍ የሚደረጉ የጋራ ትብብሮችን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋገጡ፡፡

የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በኢትዮጵያ የኮሎምቢያ አምባሳደር ከሆኑት ዬሶን አርካዲዮ ሜኔስ ኮፕቴን ጋር በአዲ አበባ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም ሁለቱ ሀገራት በትምህርቱ ዘርፍ በይበልጥ በትብብር መሥራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል በትምህርቱ ዘርፍ በትብብር ለመሥራት የሚያስችሉ ጉዳዮችን ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡

በተለይም በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ በተማሪዎች ነጻ የትምህርት ዕድል፣ በሙዚቃና ባህል ልውውጥ እንዲሁም በሌሎች ጉዳዮች በትብብር መሥራት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡

አምባሳደር ዬሶን አርካዲዮ ሜኔስ ኮፕቴ በበኩላቸው ኮሎምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን ገልጸው፤ በትምህርቱ ዘርፍም በትብብር መሥራት እንደምትፈልግ አረጋግጠዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ ነጻ የትምህርት ዕድልና የባለሙያ ልውውጥ፣ በከፍተኛ ትምህርት የሰላም ግንባታ እንዲሁም በሙዚቃና ባህል ልምድ ልውውጥ በማድረግ ረገድ በትብብር መሥራት እንደሚፈልጉ አንስተዋል።

ሁለቱ አካላት በቀጣይ በሚኖራቸው ግንኙነቶች በትምህርቱ ዘርፍ የሚደረጉ የጋራ ትብብሮችን አጠናክረው ለመቀጠል ተስማምተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.