Fana: At a Speed of Life!

ዛሬ ምሽት በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሦስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ30ኛው ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ አርሰናል በሜዳው ኢምሬትስ ምስት 3 ሰዓት ከ 45 ላይ ፉልሀምን ያስተናግዳል።

የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል ፕሪሚየር ሊጉ ለሀገራት ጨዋታ ሲቋረጥ በመጨረሻ የሊጉ ጨዋታ ቼልሲን ማሸነፉ ይታወሳል።

አርሰናል በ58 ነጥብ 2ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ÷ ተጋጣሚው ፉልሀም በ45 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስ በርስ ጨዋታዎች አርሰናል በሁለቱ ሲያሸንፍ÷ ፉልሀም በአንዱ ድል አድርጎ በሁለቱ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

ፉልሀም በሳምንቱ መጨረሻ በኤፍ ኤ ካፕ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ በክሪስታል ፓላስ ከደረሰበት ሽንፈት በኋላ ወደ ድል ለመመለስ ይፋለማል።

አርሰናል ከፉልሀም ጋር ካደረጋቸው ያለፉት 31 የሜዳው ላይ ጨዋታ ምንም ሽንፈት አላስተናገደም።

በሌላ የሊጉ ጨዋታ ኖቲንግሀም ፎረስት በሜዳው ሲቲ ግራውንድ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ማንቼስተር ዩናይትድን ያስተናግዳል።

በኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶ እየተመሩ ጥሩ የውድድር ዓመት እያሳለፉ የሚገኙት ኖቲንግሀም ፎረስቶች አራት ውስጥ ለማጠናቀቅ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ከጨዋታው ነጥብ ይዘው ለመውጣት ይፋለማሉ።

ተጋጣሚው ማንቼስተር ዩናይትድ በሊጉ በተከታታይ ጨዋታ ለማሸነፍ እና ነጥቡን ከፍ ለማድረግ ወደ ሜዳ ይገባል።

ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድር ባደረጓቸው ካለፉት አምስት የእርስበርስ ግንኙነቶች ማንቼስተር ዩናይትድ በሦስቱ ሲያሸንፍ÷ ቀሪውን ሁለት ጨዋታ ኖቲንግሀም ፎረስት ድል አድርጓል።

ኖቲንግሀም ፎረስት በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ በ54 ነጥብ 3ኛ ላይ ሲቀመጥ ማንቼስተር ዩናይትድ በ37 ነጥብ 13ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ዎልቭስን ከዌስትሀም ዩናይትድ ምሽት 3 ሰዓት ከ 45 ላይ የሚያገናኘው ጨዋታ ሌላኛው ዛሬ ምሽት የሚደረግ የሊጉ ጨዋታ ነው።

ሊጉን ሊቨርፑል በ70 ነጥብ ሲመራው፣ አርሰናል በ58፣ ኖቲንግሀም ፎረስት በ54፣ ቼልሲ በ49 ነጥብ ከ2ኛ እስከ 4ኛ ባለው ደረጃ ተቀምጠዋል።

ወራጅ ቀጠናው ላይ ኢፕስዊች ታውን፣ ሌስተር ሲቲ እና ሳውዛምፕተን ይገኛሉ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.