Fana: At a Speed of Life!

በትግራይ ክልል ለሚገኙ የጤና ተቋማት የ120 አምቡላንሶች ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በትግራይ ክልል ለሚገኙ የጤና ተቋማት 120 አምቡላንሶችን ጨምሮ የመድኃኒትና የህክምና መሳሪያዎች ድጋፍ መደረጉን በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የትግራይ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ገለጸ።

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ብርሀኑ መኮንን እንደገለፁት፤ በክልሉ ያለውን መሰረታዊ የመድኃኒት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት እና የአምቡላንስ ተደራሽነትን ለማስፋት ማህበሩ ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ድጋፍ ተደርጓል።

የ120 አምቡላንሶች ድጋፍ መደረጉ በተለይ ከወሊድ ጋር በተያያዘና በድንገተኛ አደጋ በእናቶችና ህጻናት ላይ የሚከሰት ሞትን ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የክልሉን የጤና አገልግሎትና ስርዓት ለማሻሻልም ተጨማሪ ስራዎች እንደሚጠይቅ ገልጸው፤ በገጠር አካባቢ በሚኖረው ማህበረሰብ ዘንድ ያለውን የመድኃኒትና የአምቡላንስ አገልግሎት ተደራሽነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል።

በተመሳሳይ የዓይደር ስፔሻላይዝድ ሪፈራል እና የመቀሌ አጠቃላይ ሆስፒታሎች 18 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁስን በድጋፍ መልክ አግኝተዋል።

በርክክብ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የጤና ቢሮ ተወካይ አቶ ሚኪኤለ ሃጎስ፣ ለድጋፉ አመስግነው መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እያደረጉት ያለውን መሰል ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.