ኢትዮጵያ የህብረቱ የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት የአባልነት ተግባሯን በይፋ ጀመረች
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሆና የ3 ዓመት ቆይታዋን በዛሬው ዕለት በአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደው የአቀባበል ሥነ-ሥርዓት በይፋ ጀምራለች።
በሥነ-ሥርዓቱ የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት የሚያዚያ ወር ሊቀ መንበር አምባሳደር ርቤካ አሙጌ ኦቴንጎ አዲስ የተመረጡ አባላት የአህጉሪቱን ሰላም እና ደህንነት ለማስቀጠል ባላቸው አቅም እና ልምድ ላይ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የፖለቲካ ጉዳዮች፣ የሰላም እና ጸጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዴዮዬ በበኩላቸው አዳዲስ አባላት ሲጨመሩ ምክር ቤቱ በአህጉሪቱ ግጭቶችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርገዋል ብለዋል።
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ አፍሪካ ህብረት የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ሂሩት ዘመነ ኢትዮጵያን በመወከል ተገኝተዋል።
ኢትዮጵያ ከሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ጋር በቅርበት እንደምትሰራ የተገለጸ ሲሆን፤ በግጭት አፈታት፣ በሰላም ማስከበር እና በሰላም ግንባታ ዘርፍ ያላትን ልምድ በመጠቀም ለአህጉሪቱ ሰላምና መረጋጋት የምትሰራ መሆኗ ተመላክቷል።
በ46ኛው የአፍሪካ ኅብረት መደበኛ የአስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ ወቅት ኢትዮጵያ እና ኢስዋቲኒ የህብረቱ የሰላም እና የፀጥታው ምክር ቤት አዲስ አባል መመረጣቸው ይታወሳል።