ኢትዮጵያና አውስትራሊያ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያሳድጉ የትብብር መስኮች ላይ በቅንጅት ለመሥራት ተስማሙ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የሥራ እና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ መካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ደቡብ ሱዳን የአውስትራሊያ አምባሳደር ፒተር ሃንተር (ዶ/ር) ጋር ተወያይተዋል።
ሚኒስትሯ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ÷ ከአምባሳደሩ ጋር የሁለትዮሽ ግንኙነታችን በምናሳድግበት ሁኔታዎች ላይ ውጤታማ ውይይት አካሂደናል ብለዋል፡፡
በውይይቱ ወቅት ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የተቀረፁ የልማት ፖሊሲዎችንና የተገኙ ውጤቶች ማንሳታቸውን ገልጸዋል፡፡
በክህሎትና ቴክኖሎጂ ልማት እንዲሁም ሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ እየተተገበሩ ያሉ የሪፎርም ሥራዎችን በዝርዝር መመልከታቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያና አውስትራሊያ የክህሎት ልማት እና የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችን ጨምሮ የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያልቁ የትብብር መስኮች ላይ በቅንጅት ለመሥራት መግባባታቸውንም አመልክተዋል፡፡
ይህም ረዥም ጊዜ ያስቆጠረውን የሁለትሽ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሳድገው ይሆናል ነው ያሉት፡፡
በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ፒተር ሃንተር በክህሎት ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር ለመስራት ላሳዩት ቁርጠኝነትም ምስጋና አቅርበዋል።