Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት 8 ወራት ከ264 ቢሊየን ብር በላይ ብድር ለደንበኞች ማቅረቡን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 264 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር ብድር ለደንበኞች ማቅረቡን አስታውቋል።

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቤ ሳኖ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ለመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የባንኩን የስምንት ወራት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት አቅርበዋል።

አቶ አቤ ሳኖ በዚህ ወቅት÷ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድርን ከማስፋፋት እና የዜጎችን የፋይናንስ ተጠቃሚነት ከማሳደግ አንፃር አዳዲስ የብድር አይነቶችን እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ ባለፉት ስምንት ወራት ብቻ 264 ነጥብ 65 ቢሊየን ብር ብድር ለደንበኞች ማቅረቡን ገልጸው÷ ከተሰጠው ብድር 88 ነጥብ 2 በመቶ ለግሉ ዘርፍ የተሰጠ መሆኑን አስታውቀዋል።

ጠቅላላ የተሰጠ የብድር መጠን ብር 1 ነጥብ 39 ትሪሊየን መድረሱን አስረድተዋል፡፡

የብድር ተደራሽነትን ከማስፋት አንፃር ባንኩ ከኢትዮ ቴልኮም ጋር በመተባበር በዲጂታል አማራጭ ብድሮችን እያቀረበ መሆኑንም አመልከተዋል፡፡

ባንኩ በዲጂታል አማራጭ ባለፉት ስምንት ወራት 3 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር ብድር ማቅረብ መቻሉን አንስተው÷ በዚህም እስከ ፈረንጆቹ የካቲት 28 ቀን 2025 ድረስ 717 ሺህ ደንበኞች ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

ባንኩ የዜጎችን የስራ ተነሳሽነት ከመደገፍ አንጻር ጥሩ የመስራት አቅም ላላቸው ስራ ፈጣሪዎች የብድር አገልግሎት ለመስጠት አስፈላጊውን ዝግጅት መጨረሱንም ተናግረዋል።

በዲጂታል አማራጭ የብድር አገልግሎትን ለህብረተሰቡ ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ የዝግጅት ስራዎች ተጠናቀው በሙከራ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም መግለፃቸውን ከባንኩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.