ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ እንዲጠናከር ጥሪ ቀረበ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ግንባታው ሊጠናቀቅ ለተቃረበው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ቀረበ፡፡
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፤ ለኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ ወዳጆች የግድቡ ግንባታ መሠረተ-ድንጋይ ለተቀመጠበት 14ኛ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
በመልዕክቱም፤ የግድቡ ግንባታ ለፍጻሜ መቃረቡን በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አስታውቋል፡፡
ግድቡ በመላው ሕዝብ ሁለንተናዊ ድጋፍ እየተከናወነ መሆኑ፣ ግንባታውም አንድነትን ማጠናከሩ፣ በደማቅ የዲፕሎማሲ ድል ታጅቦና የኢትዮጵያን ገፅታ በመገንባት ዘንድሮ 14ኛ ዓመቱን መያዙም ተጠቅሷል፡፡
ለዚህ ድል የበቃነው በኅብረት ችለን በመቆማችን ነው ያለው ጽሕፈት ቤቱ፤ ለሌሎችም ሀገራዊ ጉዳዮች የበለጠ በጋራ መቆም እንዳለብን ለእኛም ትምህርት ለዓለምም ምሳሌ ነው ብሏል፡፡
የሚደረገው ሁሉን አቀፍ ድጋፍም ግንባታው እስከሚጠናቀቅ ድረስ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርቧል፡፡