Fana: At a Speed of Life!

አፈ ጉባዔ አገኘሁ ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ መታደጉን ገለጹ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡ ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ ታድጓል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት አመራሮቸና አባላት”ትናንት፣ ዛሬና ነገን ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሃሳብ የለውጡን 7ኛ ዓመት አስመልክቶ የፓናል ውይይት አካሂደዋል፡፡

አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር በዚህ ወቅት÷በኢትዮጵያ መጋቢት 24 የተጀመረው ለውጥ በአይነቱ የተለየና የተሳካ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

ለውጡ ሕዝባዊ፣ ሕገ-መንግስታዊና ድርጅታዊ እንዲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የለውጥ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ለለውጡ ስኬታማነት የተወጡት ሚና በታሪክ የሚወደስ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ለውጡ ዘርፈ ብዙ ውጤቶችን ለኢትዮጵያና ለሕዝቦቿ ማስገኘቱን ጠቁመው÷ ኢትዮጵያን ከመበታተን አደጋ የታዳገ መሆኑን ተናግረዋል።

በለውጡ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲ መስኮች የተገኙ ውጤቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የጨመሩ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

ለውጡን ማስቀጠልና የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሁሉም ሃላፊነት መሆኑን የተናገሩት አፈ ጉባዔው÷ የሰላም ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን በሠላማዊ ንግግርና ውይይት ብቻ መፍታት የስልጡንነት መገለጫ መሆኑን አንስተዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ም/አፈ ጉባዔ ሎሚ በዶ በበኩላቸው÷ ለውጡ የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት ያጠናከረ እንዲሁም የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና የፖለቲካ ተሳትፎ ያረጋገጠ መሆኑን አውስተዋል፡፡

በዴሞክራሲ ሥርዓትና በተቋማት ግንባታ የመጣው ለውጥ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተቀባይነት ማሳደጉን አስረድተዋል፡፡

ህዝቡ ለውጡ የታለመለትን አላማ እንዲያሳካ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ ማቅረባቸውንም የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.