Fana: At a Speed of Life!

በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመርሲሳይድ ደርቢ ጨዋታ ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በ30ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ በመርሲሳይድ ደርቢ ሊቨርፑል ከኤቨርተን ምሽት 4 ሰዓት ላይ በአንፊልድ ሮድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ሊጉን በ70 ነጥብ እየመራ የሚገኘው ሊቨርፑል ከተከታዮቹ ያለውን የነጥብ ልዩነት ለማስፋት እና ወደ ዋንጫው የሚያደርገውን ጉዞ ለማጠናከር ይፋለማል።

በሁሉም ውድድር ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል የራቀው የሊጉ መሪ ሊቨርፑል ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በዛሬው የደርቢ ጨዋታ ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

በ34 ነጥብ 15ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ኤቨርተን በሊጉ ያደረጋቸውን ያለፉትን አምስት ጨዋታዎች አልተሸነፈም።

ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ባደረጓቸው ያለፉት አምስት የእርስ በርስ ጨዋታዎች ሊቨርፑል ሁለቱን ሲያሸንፍ ኤቨርተን በአንዱ ድል አድርጎ በሁለት ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።

ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ምሽት 3 ሰዓት ከ45 ላይ ማንቼስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሀድ ወራጅ ቀጠና ላይ የሚገኘውን ሌስተር ሲቲን ያስተናግዳል።

በ48 ነጥብ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ማንቼስተር ሲቲ በሚቀጥለዉ የውድድር ዓመት በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ለመሳተፍ በሚደረገው ፉክክር ውስጥ ለመቆየት ከጨዋታው ነጥብ ይዞ ለመውጣት ይፋለማል።

በተመሳሳይ ምሽት 3 ሰዓት ከ45 ላይ ብራይተን ከአስቶንቪላ፣ ኒውካስል ዩናይትድ ከብሬንትፎርድ፣ ሳውዛምፕተን ከክሪስታል ፓላስ እንዲሁም ቦርንማውዝ ከኢፕስዊች ታውን ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ትናንት ምሸት በተደረገ የ30ኛ ሳምንት ጨዋታ አርሰናል፣ ኖቲንግሀም ፎረስት እና ዎልቭስ ድል ቀንቷቸዋል።

አርሰናል ከፉልሀም ጋር ያደረገዉን ጨዋታ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

የመድፈኞቹን የማሸነፊያ ግቦች ቡካዩ ሳካ እና ሚኬል ሜሪኖ ሲያስቆጥሩ ፉልሀምን ከሽንፈት ያልታደገች ብቸኛ ግብ ሙኒዝ ከመረብ አሳርፏል።

በጉዳት ምክንያት ለወራት ከሜዳ ርቆ የቆየው ቡካዩ ሳካ ወደ ሜዳ በተመለሰበት ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

በሌሎች የሊጉ ጨዋታዎች ኖቲግሀም ፎረስት በአንቶኒ ኢላንጋ ብቸኛ ግብ ማንቼስተር ዩናይትድን 1 ለ 0 ሲረታ ዎልቭስ ዌስትሀም ዩናይትድን በተመሳሳይ 1 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.