Fana: At a Speed of Life!

በአብዛኛቹ የበልግ ተጠቃሚ አካባቢዎች የተጠናከረ ዝናብ ስለሚኖር ጥንቃቄ እንዲደረግ ኢንስቲትዩቱ አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በሚቀጥሉት 10 ቀናት ለበልግ ዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኞቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ተጠናክረው ስለሚቀጥሉ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አሳሰበ፡፡

ከመጋቢት 23 እስከ ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓ.ም የሚኖረውን የአየር ሁኔታ ትንበያ በተመለከተ ኢንስቲትዩት በማኅበራዊ ትሥሥር ገጹ አጋርቷል፡፡

በዚሁ መሠረት በሚቀጥሉት 10 ቀናት ለበልግ ዝናብ መፈጠር አስተዋጽኦ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች በአብዛኛዎቹ የበልግ ዝናብ ተጠቃሚ የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ በተለይም ከሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ጀምሮ ይበልጥ እንደሚጠናከሩ እና እንደሚስፋፉ የትንበያ መረጃዎች ይጠቁማሉ ብሏል፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በደቡብ ምዕራብ፣ በደቡብ፣ በመካከለኛው፣ በምሥራቅ፣ በሰሜን ምሥራቅ እንዲሁም በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች የተሻለ ጥንካሬ እንደሚኖራቸው ገልጿል፡፡

በተጨማሪም በደቡብ፣ በደቡብ ምዕራብ እና በምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የገለጸው ኢንስቲትዩቱ፤ ሕብረተሰቡ እና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መክሯል፡፡

በሌላ በኩል በሚያዝያ ወር የመጀመሪያ 10 ቀናት፤ በጋምቤላ፣ አፋር፣ ሶማሌ፣ ቤኒሻንጉልጉሙዝ እና በምዕራብ አማራ አካባቢዎች ላይ የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት ከ35 እንዲሁም በጥቂት ስፍራዎቻቸው ከ40 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.