Fana: At a Speed of Life!

መጋቢት 24 ወደ ከፍታ መውጣት የጀመርንበት ዕለት ነው- አቶ አወል አርባ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) መጋቢት 24 ቀን 2010 እንደ ሀገር ወደ ከፍታ ለመውጣት እጅ ለእጅ ተያይዘን ጉዞ የቀጠልንበት ታሪካዊ ዕለት ነው ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አወል አርባ ገለፁ።

አቶ አወል የለውጡን ሰባተኛ ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ ያለፉት የለውጥ ዓመታት ሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል እንደ ሀገር ለጋራ ብልፅግና በርካታ ፈተናዎችን በድል በመወጣት በተለያዩ ዘርፎች ስኬቶችን ያስመዘገብንበት ነው ብለዋል።

የፖለቲካ ምኅዳሩን በማስፋት እና ጉዟችንን የሚያሳልጡ የአመራር ጥበቦችን በመከተላችን ወደ ለመለመ ተስፋ መሻገር ችለናል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ አመላክቷል፡፡

የተደረገው ሁለንተናዊ ሪፎርም ነጠላ ትርክቶችን በሂደት ያከሰመ፤ በተቃራኒው ገዥ ትርክቶችን በማጽናት የኢትዮጵያን ሙሉዕ ምስል በማሳየት ኅብረ-ብሔራዊ ፌዴራሊዝም እንዲዘረጋ አድርጓል ብለዋል፡፡

“አጋር” በሚል የተዛባ ገፊ ስያሜ ከመሀል ፖለቲካ ተገልለው የነበሩ ክልሎች ዋነኛ ተዋናይ መሆን መቻላቸው የለውጡ ፍሬ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ፕሮጀክቶችን ጀምሮ መጨረስ እና ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ፣ እምብዛም ያልለሙ የነበሩ እንደ አፋር ያሉ አካባቢዎችን በማረስ ምርታማ ማድረግ መቻል፣ በዲፕሎማሲው በፉክክር እና በትብብር ድሎችን ማስመዝገብ መቻል ከፍሬዎቹ መካከል መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይ እስከ አሁን ከመጣንበት አመርቂ ድል የበለጠ ለማስመዝገብ በጋራ ጥረታችንን ማጠናከር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.