የልማት ሥራዎች የከተማችንን የብልጽግና ተምሣሌትነት አረጋግጠዋል- አቶ ጃንጥራር
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) በለውጡ ዓመታት በአዲስ አበባ የተከናወኑ የልማት ሥራዎች የከተማዋን የብልጽግና ተምሣሌትነት አረጋግጠዋል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር ዓባይ ገለጹ፡፡
ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን ሰባተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ “ትናንት፣ ዛሬ እና ነገ ለኢትዮጵያ ልዕልና” በሚል መሪ ሐሳብ በዓድዋ ድል መታሰቢያ የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡
አቶ ጃንጥራር በዚሁ ወቅት፤ በፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ፣ በዲፕሎማሲ፣ በቴክኖሎጂ እንዲሁም በሰው ተኮር ሥራዎች የሀገርን ትልም የሚያሳኩ ለውጦችና ድሎች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት ሰባት የለውጥ ዓመታት የተከናወኑ የልማት ሥራዎችም የመዲናዋን የብልጽግና ተምሣሌትነት በተግባር ያረጋገጡ ናቸው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የመዲናዋን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት በተግባር ያረጋገጡና የከተማዋን ገጽታ የቀየሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡