10ኛው የክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች ዋና ኦዲተሮች ውይይት በድሬደዋ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) 10ኛው የክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤቶች የምክክር እና የልምድ ልውውጥ መድረክ በድሬደዋ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የድሬደዋ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ፋኪያ መሐመድ በዚህ ወቅት÷የጋራ ምክክሩ ደረጃውን የጠበቀ የኦዲት ተግባራት በማከናወን የመንግስትና የህዝብ በጀት በአግባቡ ለታለመለት ተግባር እንዲውል የሚያስችሉ ግንዛቤዎችን ለማሳደግ ያግዛል ብለዋል።
የልምድ ልውውጡ ደረጃውን የጠበቀ የክዋኔ ኦዲት ለመተግበር የሚያስችል ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም በየደረጃው በሚገኙ ተቋማት ውስጥ የተጠያቂነት ሥርዓትን ይበልጥ ለማጠናከር የሚያስችል መደላድል እንደሚፈጥር ነው የገለፁት፡፡
በውይይቱ ላይ የድሬደዋ አስተዳደር ምክርቤት አፈጉባዔ ፈትሂያ አደን፣ የየክልሎች እና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ዋና ኦዲተሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ፡፡
ለሶስት ቀናት በሚዘልቀው ውይይት ላይ ለተሞክሮ የሚያግዙ የተለያዩ ሰነዶች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግ መጠቆሙን የዘገበው ኢዜአ ነው።