የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ የንግዱን ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ነው -ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ተገማች የንግድ ስርዓት በመፍጠር የንግዱን ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የንግድ ፖሊሲ ረቂቅ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ወዲህ በወጪና ገቢ ንግድ ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል።
መንግሥት የተለያዩ የአሰራር ማሻሻያዎች በማድረግ ተወዳዳሪ፣ ተገማች እንዲሁም ቀጣናውን በንግድ የሚያስተሳስሩ ሰፋፊ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል መሆን የሚያስችላትን በቂ ዝግጅት በማድረግ በበርካታ መለኪያዎች ተቀባይነት ማግኘት የሚያስችላት ድርድር ማድረጓን አንስተዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በአዋጅ ተቋቁሞ በአዲስ ከተደራጀ በኋላ የንግዱን ከባቢ ምቹ የሚያደርጉ ርምጃዎች ተወስደዋል ብለዋል።
በበርካታ ሂደቶች የተዘጋጀው የኢትዮጵያ ንግድ ፖሊሲ የንግዱን ማህበረሰብ የመደራደር አቅም በማጎልበት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን የሚያሳድግ መሆኑን ተናግረዋል።
ረቂቅ ፖሊሲው ብዝኃ ዘርፍ የወጪ ንግድን ለማሳለጥ አጋዥ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡