ሀገራዊ ለውጡ በሀገር ባለቤትነት ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም መያዝ አስችሏል – እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡ የመሀልና የዳር የፖለቲካ እሳቤን በማክሰም በሀገር ባለቤትነት ጉዳይ ላይ የጋራ አቋም መያዝ አስችሏል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 7ኛ ዓመት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፥ ለውጡ የሚመራበት ትክክለኛ ፕሮግራምና አስተሳሰብ በመቅረጽ በርካታ ውጤቶች መመዝገባቸውን አንስተዋል፡፡
የፖለቲካ ሪፎርም መደረጉንና ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በጋራ መስራት የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለውጡ የመሀልና የዳር የፖለቲካ እሳቤ እንዲከስም ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
በዴሞክራሲ ሥርዓት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አዋጆችና ደንቦች መሻሻላቸውንና የጸጥታና የደህንነት መዋቅሮች የሀገርና የሕዝብ አገልጋይነት ሚናቸው ከፍ እንዲል መሰራቱን አስረድተዋል።
በኢኮኖሚ ላይ የተደረገ ማሻሻያ የለውጡ ትሩፋት መሆኑን ገልጸው፥ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት መሸጋገር የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው፥ ከተሞች ለሕዝብ መኖሪያነት ምቹ ለመድረግ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ ባለፈ የገቢ አቅምን ለማሳደግ የላቀ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል፡፡
ከለውጡ ወዲህ የተቋማትን አገልግሎት ዲጂታላይዝ ለማድረግና በሀገሪቱ ያሉትን ጸጋዎች በመጠቀም በሙሉ አቅም የማምረት ስሥ እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
ቁርሾ ከሚፈጥሩና ሰላምን ከሚያደፈርሱ አጀንዳዎች በመውጣት በልማት ላይ ማተኮር እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡