Fana: At a Speed of Life!

ሀንጋሪ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባልነት ራሷን አገለለች

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀንጋሪ ከዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አባልነት መውጣቷን አስታወቀች፡፡

ሀንጋሪ ከአይሲሲ አባልነቷ የመውጣት ውሳኔዋን ያሳለፈችው በተቋሙ የእስር ማዘዣ የወጣባቸው የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ናታኒያሁ በሀገሪቱ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እያደረጉ ባለበት ወቅት ነው።

አይሲሲ በጠቅላይ ሚኒስትር ኔታኒያሁ እና የእስራኤል መከላከያ አዛዥ በነበሩት ዮአቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ ያወጣው የእስራኤል ሃማስ ጦርነትን ተከትሎ ደርሷል ባለው ጉዳት የተነሳ መሆኑ ይታወሳል።

አይሲሲ በእስራኤል ባለስልጣናት ላይ የእስር ማዘዣ እንዳወጣ የሀንጋሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክተር ኦርባን በመንግስታቸው ሥም የእስራኤል አቻቸው ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ሀገራቸውን እንዲጎበኙ ግብዣ ማቅረባቸውን የቢቢሲ ዘገባ አስታውሷል።

በዚህም የተነሳ የአይሲሲ መስራችና አባል የሆነችው ሀንጋሪ የእስር ማዘዣ የወጣባቸውን ኔታኒያሁን አሳልፋ ተቀብላ ከማስተናገድ ባለፈ በአይሲሲ አባልነት እንደማትቀጥል ይፋ አድርጋለች።

125 አባላት ካሉት አይሲሲ በመልቀቅ ከአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መካከል ሀንጋሪ የመጀመሪያዋ መሆኗ ተገልጿል።

አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ በርካቶች የአይሲሲ አባል እንዳልሆኑ ይታወቃል።

በሚኪያስ አየለ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.