የዓለም ጂኦ ፖለቲካ ታሳቢ ያደረገና ለለውጥ የሚተጋ ወጣት አመራር ማፍራት ይገባል – ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) ተለዋዋጩን የዓለም ጂኦ ፖለቲካ ታሳቢ ያደረገ እና ለለውጥ የሚተጋ ወጣት አመራር ማፍራት ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ ገለፁ።
በአዲስ አበባ ዓድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ በሚገኘው የፓን አፍሪካ ወጣቶች አመራር ጉባኤ ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ ባስተላለፉት መልዕክት፤ አፍሪካ ራሷን ከቅኝ ግዛት ለማላቀቅ ለነፃነትና ለእኩልነት ታግላለች ብለዋል።
ይህ ትግል በታላላቅ የአፍሪካ መሪዎች ውጤት ማምጣቱን ገልፀው፤ ለአፍሪካ ህብረት መመስረትም መነሻ እንደነበር አስታውሰዋል።
የአፍሪካ አባቶች ለነፃነትና ለእኩልነት የከፈሉትን ዋጋ ወጣቱ በጥበብና በዕውቀት ላይ የተመሰረተ ልማትና ሰላም በማስመዝገብ ሊደግመው ይገባል ነው ያሉት።
ስራ አጥነት፣ የአየር ንብረት ለውጥና የፖለቲካ አለመረጋጋትን ለመፍታት ወጣቶች በዕውቀትና በጥበብ የታገዘ እገዛ መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ወጣት አመራሮች ተለዋዋጭ ለሆነው የዓለም ጂኦ ፖለቲካ የሚመጥን ሀሳብ ማፍለቅና ውሳኔ መስጠት እንደሚጠበቅባቸ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
ለአፍሪካ የሚያስፈልጋት ትብብርና በጋራ መስራት መሆኑን ጠቅሰው፤ በዚህ ረገድ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) የመደመር እሳቤን ተግባራዊ ማድረግ ውጤታማ ያደርጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተፅዕኖ ለመቋቋም የአረንጓዴ አሻራ መርኃ ግብርን ተግባራዊ ማድረግ መጀመራን፣ በምግብ ራስን ለመቻል የሌማት ትሩፋት መርኃ ግብር ተግባራዊ በመደረጉ በርካታ ውጤቶችን እያስመዘገበች መሆኗን ተናግረዋል።