የአውሮፓ ህብረት ለኢትዮጵያ 240 ሚሊየን ዩሮ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 25፣ 2017 (ኤፍ ኤም ሲ) የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ለስድስት የልማት መርሃ ግብሮች የሚውል የ240 ሚሊየን ዩሮ (32 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር) ድጋፍ አደረገ፡፡
የድጋፍ ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴና በኢትዮጵያ የህብረቱ ተወካይ አምባሳደር ሶፊ ኢመስበርገር ተፈራርመዋል።
ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት፥ ድጋፉ ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እያደረገች ባለችበት ወቅት የተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
አምባሳደር ሶፊ ኢመስበርገር በበኩላቸው፥ ድጋፉ ከሁሉም የህብረቱ አባል ሀገራት የተሰበሰበ መሆኑን ጠቅሰው፥ የኢትዮጵያን ልማትና ኢኮኖሚ እንደሚውል ገልጸዋል።
ድጋፉ የዴሞክራሲ ተቋማትን ለማጠናከርና የሽግግር ፍትሕ ሂደቱን ለመደገፍ እንዲሁም የሥርዓተ ፆታ እኩልነትና ማህበራዊ ትስስርን ለማሳደግ እንደሚውል ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም የዴሞክራሲ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተከሰቱ ግጭቶች ማገገሚያ የሚሆን ነው ተብሏል፡፡
በዘመን በየነ